የጉራጌ ባህልና እሴቶች በሀገርና በአለም አቀፍ ደረጃ የበለጠ ለማስተዋወቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ።


መምሪያው የ2016 ዓ.ም የ6ወር እቅድ አፈጻጸም ከወረዳና ከከተማ አስተዳድር የተቋሙ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ ገምግሟል።

የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ መሰረት አመርጋ እንደተናገሩት የጉራጌ ብሔር በድምቀት ከሚያከብራቸው በዓላት የመስቀልና የአረፋ ክብረ በዓላት ተጠቃሾች ሲሆኑ በዓላቱ ይበልጥ እንንዲተዋውቁ በየዓመቱ በፌስቲቫል ደረጃ እየተከበሩ ይገኛል።
እንደ ኃላፊዋ ገለጻ የ2016 የመሰቀል በዓል የውጭ ሀገር እና የሀገር ውስጥ ቱሪስቶች እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላት በተገኙበት በድምቀት ማክበር ተችሏል።

የጉራጌ ልዩ ክትትፎ፣ የዳኝነት ስርአት፣ የመንደር አመሰራረትና የቤት አሰራ በዩኒስኮ እንዲመዘገቡ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን ሰፊ ስራ እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

አክለውም የጉራጌ አንድነት የበለጠ እንዲጠናከር ከጉራጌ ዞንና ከምስራቅ ጉራጌ ዞን አስተዳደሮች በጋራ በመሆን የጉራጌ የባህል ሸንጎ እንዲጠናከርና ባህልን ለማስተዋወቅ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸው ተናግረዋል።

የጉራጊኛ ቋንቋ የስራ ቋንቋ እንዲሆን እየተሰራ ነው ያሉት ወ/ሮ መሰረት ለዚህም ምክር ቤቶችና የተለያዩ ሁነቶች በጉራጊኛ ቋንቋ እንዲከናንኑ ሁሉም ባለበት አካባቢ ለቋንቋው ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ መክረዋል።

የጉራጊኛ ቋንቋ እንዲያድግ ህጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ በተደረገው ጥረት በአሁን ሰአት በ1ኛ ክፍል ደረጃ ማስተማር ተጀምሮ ውጤት እያስገኘ ሲሆን ቋንቋውን ይበልጥ እንዲጎለብት የሚዲያ ቋንቋ ለማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።

የጉራጌ ባህልና እሴቶች በሀገርና በአለም አቀፍ ደረጃ የበለጠ ለማስተዋወቅ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነ አስታውቀዋል

ወ/ሮ መሰረት አክለውም በዞኑ የቱሪዝም ዘርፉ መነቃቃት የታየ ሲሆን በዞኑ ያሉ ሰፋፊ የቱሪዝም ሀብቶቻችን በአግባቡ በመጠቀም የኢኮኖሚ ማስገኛ እንዲሆኑ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።

በእነዚህ የቱሪስት ሰጪ አገልግሎት ተቋሟት ላይ ባህልን የበለጠ ማስተዋወቅ ያስፈልጋል ያሉት ኃላፊዋ ጀፎረዎች እና የቱሪዝም ስፍራዎች የይዞታ ማረጋገጫ እንዲኖራቸው መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በየ መዋቅሩ ያሉ የስነ-ጹሁፍ ክበባት ፣የሀገርህን እወቅ እንዲሁም አማተር ከያኒያን፣ ሳምንታዊ የቋንቋ ቀን ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ወ/ሮ መሰረት አሳስበዋል።

አቶ ግዛቸው ውጅራና ወ/ሮ የሺነሽ ተካ የውይይቱ ተሳታፊዎች ሲሆኑ በባህል፣በቋንቋ በቱሪዝምና በሌሎች ዘርፎች በርካታ ስራዎች እየሰሩ እንደነበር ገለጸው የጉራጌ ባህልና እሴት ተጠብቆ እንዲቆይ እንዲተዋወቅና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርጉ ስራዎች ሲሰሩ እንደነበር ተናግረዋል።

አክለውም ባህላዊ የእደ ጥበብ ስራዎችን እንዳይጠፉ ከማድረጉ በተጨማሪ በዘርፉ የተሰማሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ መሆናቸው በመጠቆም።

ከዚህ በፊት ያልተከናወኑ ተግባራት ለይቶ በመያዝ የባህልና ቱሪዝም ስራዎች እንዲተዋወቁና ጎልተው እንዲወጡ የሚዲያ ስራ ላይ የበለጠ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *