የጉራጌ ቀዬ እጁን ዘርግቷል።እኖር ‘ነዎር’ ብሎ ሰው እየጠበቀ ነው።


(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም – ለድሬ ቲዩብ)

(ተጓዡ ጋዜጠኛ ጉራጌ ምድር ገብቷል። የጉራጌ ቀዬ እንግዳ ለመቀበል “የተንቢ” እያለ ነው ይለናል። እኖር ደርሼ የጉንችሬን ዙሪያ ገባ ማሰስ ጀመርኩ ሲል ትረካውን ይጀምራል።)
መስከረም ሁለተኛ ሳምንት ኾነ። ድባቡ ልዩ ነው። ጉራጌዎች ቀዬ ገብቻለሁ። እኔም እንደ ጉራጌ የዓመት የምርቃት ስንቄን የምሸምትበት መስቀል እንኳን ደህና መጣ።

እኖር ነኝ። ጉንችሬ መስቀልና አረፋ ነፍስም አይቀርላት። ሽር ብትን ትላለች። ከአዲስ አበባ 198 ኪሎ ሜትር ተጉዣለሁ።

እኖር ነዎር ብሎ ሰው እየጠበቀ ነው። መንደር ከመቀመጫው ተነስቶ ወገን “እንኳን ደህና መጣህ” የሚልበት ቀዬ። ጀፎረው ለእናንተ የተዘረጋ እስኪመስላችሁ ልባችሁን በሀሴት መንፈስ የሚሞሉ መንደሮች፤
ወደ መስቀል ስትመጡ ከየጎጆው ውጡ። አውቃለሁ የጉራጌ ጎጆ ዓለም ነው። አውቃለሁ ቅጥሩ ዓለምን ያስረሳል። ደግሞም ይገባኛል እንዴት ከዚያ ድባብ ይወጣል? ግን ውጡ። ደግሜ እላችኋለሁ ወጡና ወደአካባቢያችሁ ቅጥር ዙሩ።

እናንተ የጉራጌ ልጆች በእርግጥ ቀዬውን ታውቁታላችሁ፣ ግን የልጅነታችሁን ትዝታ ዳግም አጣጥሙት፤ ምድሩን ጎብኙ፣ ወደ መስኩ ውጡ፣ ወደ ደኑ ዝለቁ።

እናንተም የጉራጌ እንግዳ የኾናችሁ የሀገሬ ልጆች ጉራጌ ቀዬ ስትደርሱ እንዲሁ አትመለሱ። እንዴ! ዙሪያ ገባውንም እዩት፣ ጉራጌን በቤቱ ብቻ ሳይኾን በቀዬውም እወቁት፤ ፀጋዎቹን ጎብኙ፣ የሰላምን ጥቅም አጣጥሙት፣ የባህል ጉልበት ምስክር ትሆናላችሁ።

እንደ ንጉሥ አሹወ እንደ ባሺ ኤገኖ ምድሩን ግዙት። ወደ ኮረብታዎቹ ከፍ በሉ። ወንዞቹን አግኟቸው፣ በጀፎረው ዘንጡበት፣ ወደ ታሪካዊ መካናቱ ግቡ በሁሉም የጉራጌ ምድር ድንቅ ትመለከታላችሁ።

እኖር ኮሰድ ቀበሌ ደርሻለሁ። የተፈጥሮ ደን ልጎበኝ ቀበሌዋ በፍቅር ተቀበለቺኝ። ወደ ደኑ ገባን። የደኑ ስም የኮሰድ ጥብቅ ደን ይባላል። በእርግጥም ለጉንችሬ ሰባት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይሄንን ማየት ልዩ ስሜት አለው።

ሀገር በቀል ዛፎች የሞሉበት፣ በተንዠረገጉ የብሳና ዛፎች ጥድ እየታከክን አለፍን። ስለ ጉራጌ ምድር ውበት አለማውራት ከጡር ይከፋል።

የሸበቱ እንጨቶች፣ ያረገረጉ የሳር ጎዳናዎቹ፣ ምንጭ የሚለግሱ መሬቶች ሁሉን እያለፍኩኝ ገሰገስኩ። አንድ ድምፅ ተቀበለኝ። የፏፏቴ ነው። ድምፁ ቢቀርብም ጥቅጥቁ ደን የምሰማውን አላሳየኝም ነበር።

በመጨረሻ አየሁት፤ ኮሰድ ፏፏቴ። የዋሻ በራፍ ላይ እንደ መጋረጃ የተሰቀለ ተፈጥሮ። ወደ ፏፏቴው ቀረብኩ፣ ወደ ጊቤ ከመዋሃዳቸው በፊት በጉራጌ ምድር እንዲህ ያለ ውበት ፈጥረው የሚያልፉ የቀዬው ወንዞች ብዙ ናቸው። እንኳን መጣሁ፤ የጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያን አመሰግናለሁ። እነ መሰረት አመርጋ ደግሞ ይሄንን እየው ባይሉኝ፤ ባልመጣ ይሄን ውብ ደን የት አየው ነበር? ለዚህ ነው የደረሳችሁበትን የጉራጌ ቀዬ ዙሪያ ገባ ፈትሹ የምላችሁ።

እኖር ብቻ እኮ አይደረስም። የዋሻዎች ቀጠና፤ የነ ጓንታና፣ የነ ጌንደረድ፣ የበርገዛ፣ የነ አጋሬ፣ የእነ ጓጅ፣ የነ ሲከምሰር…..ደከመኝ።
ደግሞ ፏፏቴውስ ከ ሲከምሰር እስከ ሻፏሞ፣ ውቦቹ እነ ኩነበር፣ እነ ሙጃን፣ እነ ባጣውና፣ እነ ገረንቦ፣ እነ ጌንድረድ ላልዘልቀው የፏፏቴ ስሞች ጀመርኩ፤ የፏፏቴ ምድር ብለውስ?

ወደ ዋሻው ወጣሁ። ስፋት አለው። ደጃፉ የውሃ መጋረጃ የለበሰ፣ የአርበኝነት ዘመን ታሪክ የታተመበት፣ ተፈጥሯዊ ግን ደግሞ የሰው አሻራም ያረፈበት።

የሚገርመኝ በዚያ በተጣበበ መሬት ሰፊ ቁጥር ያለው ህዝብም ኾኖ ጉራጌ ተፈጥሮ መጠበቅ ይችላል። ደጃፉ ላይ እንዲህ ያለ ዱር ቀጥሮ ይኖራል። እንደ ትሪሚንግሃም ጉራጌ ብልህና ታታሪ ሰራተኛ ነው ብዬ አልነግራችሁም። ይልቁንስ ይሄንን ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለዓለም ይነግራል። የሚገርመኝ ነው ያልነው ህዝብ የማያሳፍር ብርቱ መኾኑ ነው።
ገና መች ቆምን እኖር ወደ ካናስ እንዘልቃለን። ጋሀራድ ትቀበለናለች። እስቲ አረቅጥ ደረስ ብዬ ልምጣ። ጉመር ጎራ ብዬ አለቅጥን እጎበኛለሁ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *