የጉራጌ ማህበረሰብ አንድነት ይበልጥ በማጠናከር የህብረተሰቡ ሰላም ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ የጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ አስተዳደር አስታወቀ።

የጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ አንደኛ መደበኛ ጉባኤውን በቡታጅራ ከተማ ተካሄደ።

በዚህም ጉባኤ የጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ መተዳደሪያ ረቂቅ ደንብ በጉራጌ ዞን ፍትህ መምሪያ ቀርቦ በጉባኤው ተሳታፊዎች ውይይት ከተደረገበት በኋላ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል።

በጉባኤው ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል በዞኑ በርካታ ትላልቅ የሀገር ሽማግሌዎች የሚገኙ መሆኑን ገልጸው እነዚህን አባቶች በመጠቀም በየአካባቢው የሚገኙ ባህላዊ ሸንጎዎች እንዳሉ ሆነው የማህበረሰቡ አንድነት ይበልጥ ለማጠናከር አንድ የባህል ሸንጎ አስተዳደር በመመስረት ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ እንዲገባ አባቶች ያደረጉት ጥረት አበረታች ነው ብለዋል።

ባህላዊ ሸንጎ መጠናከር የህዝብ ለህዝብ ትስስርና አንድነት ይበልጥ ለማጠናከር ሚናው ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው የሽምግልናው ስርዓት ባህላዊ ዕሴቱን በጠበቀ መልኩ ሊመራ እንደሚገባም ተናግረዋል።

አክለውም ባህላዊ ሸንጎውን በማጠናከር ወጤታማ ተግባራት ማከናወን እንዲችል አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ ለማድረግ የዞኑ አስተዳደር በትኩረት እንደሚሰራ አቶ መሀመድ ጀማል ተናግረዋል።

የጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ አስተዳደር ምክትል ሰብሳቢ አቶ ጸጋዬ ታቦር በበኩላቸው ከዚህ ቀደም የዘቢደር ተራራ አስፋልት ከመሰራቱ በፊት ጉራጌ ምስራቅና ምዕራብ እየተባለ ለሁለት ከፍሎት እንደነበር አስታውሰው ይህን ችግር መንገድ በመሰራቱ እንደተቀረፈ ሁሉ አንድነቱ ለማጠናከር ባህላዊ የአስተዳደር ሸንጎ በመመስረት ጥሩ እንቅስቃሴ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

ይህንንም የጎርደነ ሴራ፣ የፈራገዘኘ ሴራ፣ የጆካ ሴራና ስናኖ ሴራ የራሳቸው የሆነ መተዳደሪያ ደንብ ቢኖራቸውም የጉራጌ አንድነት ይበልጥ ለማጠናከር ሁሉንም ቤተ ጉራጌ ያካተተ አንድ ባህላዊ ሸንጎ የዛሬ አመት መመስረቱና ወደ ስራ መገባቱን ተናግረዋል።

ባህላዊ ሸንጎው የራሱ መተዳደሪያ ደንብ ያለው መሆኑን የገለጹት አቶ ጸጋዬ ይህንን መሠረት በማድረግ በህብረተሰቡ መካከል ጨለማ ተገን በማድረግና ማስረጃ አጥፍቶ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እና በመደበኛው የህግ ተቋማት ለመዳኘት የማይመቹ ጉዳዮችን በመዳኘት ተበዳይ ፍትህ እንዲያገኝ በማድረግ የማህበረሰቡን ችግር ይቀርፋል ሲሉ ገልጸዋል።

የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ተመሰገን ገብረመድህን እንደገለጹት ጉራጌ የማንነቱ መገለጫ የሆኑ ቱባ ባህላዊ እሴቶችን ሳይበረዙ ተንከባክቦ በማቆየት ለተተኪው ትውልድ ለማሸጋገር የባህል ሸንጎ የሚያደርገው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው።

የጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ በዞኑ ውስጥና ውጪ የሚፈጠሩ የማህበረሰቡ ችግሮች ለመቅረፍ ከሌሎች አቻ ባህላዊ ሸንጎዎች ጋር ትስስር በመፍጠርና ልምድ በመውሰድ የተሻለ አቅም እንደሚፈጥሩ አቶ ተመስገን ተናግረዋል ።

የጉባኤው ተሳታፊ አባቶች በሰጡት አስተያየት የጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ በየአካባቢው የሚፈጠሩ ችግሮችን በመቅረፍ የህዝቡ አንድነት ለማጠናከር በትኩረት እየሰራ ነው ብለዋል።

አክለውም የጉራጌ ባላዊ ሸንጎ ተመስርቶ አንደኛ መደበኛ ጉባኤው ማካሄድ መቻሉን እንዳስደሰታቸው ገልጸው በቀጣይነትም ባህላዊ ሸንጎውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በመጨረሻም የጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ መተዳደሪያ ረቂቅ ደንብ በጉራጌ ዞን ፍትህ መምሪያ አቃቢ ህግ በሆኑት በአቶ አብድልመናን ዲኖ ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኋላ በሙሉ ድምጽ ጸድቋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

= ኢትዮጵያን እናልማ!
= የፈረሰውን እንገንባ!
= ለፈተና እንዘጋጅ!

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *