የጉራጌ ዞን አስተዳደር ከጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ጋር በመተባበር የጉራጌ የባህል ሸንጎ 2ኛ አመት መደበኛ ጉባኤ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በጉባኤው ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት የጉራጌ ማህበረሰብ ከጥንት ጀምሮ የራሱ የሆነ ታሪክ፣ ባህል፣ ቋንቋና ጠንካራ የፍትህና የዳኝነት ስርዓት፣ ጠንካራ የስራና የቁጠባ ባህል፣ የአብሮነትና የመቻቻል እሴቶችን ባለቤት በመሆኑ እነዚህን ሀገር በቀል እውቀቶችን በተገቢው ጠብቆ እና ተንከባክቦ ለትውልድ ከማስተላለፍ አንጻር እየተሰሩ ያሉ ስራዎች በቀጣይ ተጠናክረው መቀጠል አለበት ብለዋል።
ሸንጎው ያወጣቸውን ደንቦችን ተግባራዊ እንዲሆኑ አስተዳደሩ የበኩሉ እገዛ እንደሚያ ገልጸው የጉራጌ አንድነት ሰላም እና እድገት ይበልጥ እንዲጠናከር ከማድረግ ባለፈ ከሌሎች ብሔረሰቦች ጋር ያለውን አብሮነትና አንድነት ማጠናከር ይገባል።
ባህላዊ ሸንጎው በዞኑ የሚፈጠሩ የተለያዩ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን በጥበብ በመፍታት የተደበቁ ወንጀሎችን በብቃትና በብልሃት በማውጣት የጋራ እሴቶችን አጠናክሮ የህዝቡን አብሮነትና አንድነት በማጠናከር ረገድ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በ2013 ዓ.ም ጀምሮ በየአከባቢው በተበታተነ መንገድ ሲመራ የነበረው ሸንጎ ዞናዊ ተደርጎ አንድ ጠንካራ ሸንጎ መመስረቱ የበለጠ ጠንካራና ተደማጭ እንዲሆን ከማድረጉም ባለፈ የጋራ እሴቶቻችንን በሀገር አቀፍ እና በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና እንዲያገኝ ትልቅ ፋይዳ እንዲኖረው እንደሚያደርግም ገልጸዋል።
ሸንጎው ጠንካራ ገለልተኛ ከየትኛውም የፖለቲካ ጫና ነጻ ሆኖ ራሱን የሚያስተዳድር ሆኖ ለቀጣይ ትውልድ ደማቅ ታሪክ የሚጽፍ እንዲሆን የዞኑ መንግስት እገዛ እንደሚያደርግ ገልጸው ከዚህም ባለፈ የወልቂጤ ዩንቨርስቲ ምሁራን፣ የጉራጌ የልማት ማህበር፣ አመራሮችና ባለሀብቶችን ሸንጎው መደገፍ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የጉራጌ ሸንጎ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ጸጋዬ ታቦር እንዳሉት የጉባኤው አላማ ሸንጎው ያቀዳቸውንእቅዶችን እስከታች በማውረድ ማህበረሰቡ ንቁ ተሳትፎ በማድረግና ከመንግስት ጎን በመቆም ለሰላምና ለልማት እንዲነሳሳና ባህሉና ቋንቋውን ለማጠናከር ያለመ ነው።
የጉራጌ ሸንጎ ያወጣቸውን ደንቦችን በተለይም በጋብቻና በለቅሶ ወቅት የሚወጡ ከፍተኛ ወጪዎችን ለማስቀረት ደንቦች ቢወጡም ተፈጻሚ ከማድረግ አንጻር ውስንነት መኖሩን ጠቁመው እነዚህን ተፈጻሚ እንዲሆኑ ከወረዳ አመራሮችና ከባህል ቱሪዝም ጽ/ቤት አመራሮችና ከዞኑ አስተዳደር ጋር በመሆን ችግሩን ለመቅረፍ እንደሚሰራም ጠቁመዋል።
በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶችንና አለመግባባቶች ለአብነትም በወልቂጤና በጉንችሬ ከተማ ተፈጥሮ የነበረው አለመግባባቶችን ለመፍታት ሸንጎው በትከረት ሲሰራ መቆየቱንም በሪፖርቱ ተመላክቷል።
በቂጫ/ሴራ በሀገር ሽማግሌዎች የሚወጡ በማህበረሰቡ ዘንድ አላስፈላጊ ወጪዎችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን ለማህበረሰቡ ጠቃሚ ደንቦችና መመሪያዎችን አተገባበር ላይ ክትትል በማድረግ የእርምት እርምጃ ወስዷል።
በ2016 በጀት አመት የማህበረሰቡ አንድነት የሚያጠናክር አመታዊ ፈቸት/ኬርታ/ዱአ ፕሮግራም እንዲዘጋጅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን መስራት፣
በዞኑ የሚገኙ የጉራጌ፣ የቀቤናና የማረቆ ባህላዊ የዳኝነት ስርአቶችን ለማጠናከርና ዞናዊ የህዝቡን አንድነት ማረጋገጥ የሚያስቻል ዞናዊ የባህል ሸንጎ መመስረት የሚያስችሉ ስራዎችን ለመስራት ታቅዷል።
የጉራጌ የባህል ሸንጎ በዞኑ ምክርቤት መጽደቁን አስታውሰው በቀጣይ በጀት አመት በደቡብ ክልል ምክር ቤት ለማጽደቅ በእቅድ መያዙንም ገልጸዋል።
የጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወይዘሮ መሰረት አመርጋ በበኩላቸው ሸንጎው የማህበረሰቡን አንድነት የሚያስቀጥል ጠንካራ እንዲሁም ገለልተኛ የሆነ ሸንጎ እንዲሆንና የማህበረሰቡን ሰላምና ልማት የሚያረጋግጥ እንዲሆን ሁሉም ማገዝ ይኖርበታል።
በቀጣይ በጀት አመት በዞኑ የሚገኙ የጉራጌ፣ የቀቤናና የማረቆ ብሔር ብሔረሰቦችን ዞናዊ ሸንጎ ለመመስረት በሚደረገው ጥረት መምሪያው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እንደሚሰራም ገልጸዋል።
የጉባኤው ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የጉራጌ ሸንጎ የማህበረሰቡን የስራ ባህል፣ አንድነቱንና አብሮ የመኖር እሴቶችን ከማስቀጠል ጎን ለጎን ልማቱን እንዲረጋገጥ በትኩረት መስራት እንዳለበት ገልጸዋል።
ሸንጎው ያወጣቸውን ደንቦችን ተፈጻሚ እንዲሆኑና ሸንጎው ይበልጥ እንዲጠናከር የሚመለከታቸው አካላት ሁለንተናዊ ድጋፍ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል።
በመጨረሻም የሸንጎው የ2015 በጀት አመት ሪፖርትና የ2016 ዓ.ም ጠቋሚ እቅድ ቀርቦ ውይይት ከተደረገበት በኃላ ጸድቋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።