የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ እንዳሻው ጣሰው እንዳሉት ሰላም ለሁሉም ነገር መሰረት በመሆኑ ቅድሚያ የአካባቢያችንና የሀገራችን ሰላም እንዲረጋገጥ አበክረን ልንሰራ ይገባል ብለዋል።
ከዚህ በፊት በተደረጉ የአረንጓዴ አሻራ እንቅስቃሴዎች የአፈርና ውሃ ጥበቃችንና የአየር ንብረት ለውጥን መዛባት ማስተካከል የተቻለ ሲሆን በቀጣይም ጀፎረን ጨምሮ የፍራፍሬ ችግኞች በመትከል የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተናግሯል።
የህብረተሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ሊያረጋግጡ የሚችሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን በመትከል ሀገራችን ከተረጂነት ነጻ እንድትወጣ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።
የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ እንደተናገሩት ችግኝ መትከል ሰላም፣ አንድነት፣ ፍቅር፣ አብሮነት፣ ተስፋና የመጪው ትውልድ ህልውና እየተከልን መሆኑን አስገንዝበዋል።
በጉራጌ ዞን በየ አመቱ ለችግኝ ተከላ ልዩ ትኩረ ተሰጥቶ በመሰራቱ የደን ሽፋን በአሁን ሰአት 24 ከመቶ ማሳደግ ተችሏል ያሉት አቶ አበራ በየአመቱ የሚተከሉ ችግኞች የጽድቀት መጠናቸው 89 ከመቶ እንደሆነ አስታውቀዋል።
በዚህም የተጎዱ መሬቶችም ወደ ምርት ሰጪነት እንዲገቡ እና በየጊዜው የደን መሬት መፍጠር መቻሉ ገልጸው የተመቻቸ ሀገር ለትውልድ ለማስተላለፍ የአካባቢ ጥበቃና እንክብካቤ ስራ ከመቼውም ጊዜ በላይ ማጠናከር ያስፈልጋል ብለዋል።
በዛሬው እለትም በ10 ሄክታር መሬት እስክ 20 ሺህ የሚደርሱ ችግኞች መትከል እንደተቻለ አመላክቷል።
የኢፌድሪ ህብረት ስራ ኤጀንሲ ምክትል ዳይሬክተር እና የጉልባማ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሺሰማ ገ/ስላሴ እንደገለጹት ልማት ማህበሩ ለህብረተሰቡ የውሃ፣ የትምህርት የጤናና ሌሎች በርካታ የልማት ችግሮች ለመቅረፍ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በየአመቱ የችግኝ ተከላ ጉዞ መደረጉ የከተማና የገጠሩ ህብረተሰብ ግንኙነት የበለጠ እንዲጠናከር ያደርጋል ያሉት አቶ ሺሰማ በተጨማሪም አዳዲስ አባላት የሚፈሩበት፣ የብሄሩ የእንግዳ ተቀባይነት ባህል የሚታይበት፣ ወንድማማችነትንና እህተማማችነት የበለጠ የሚጠናከርበት እና ሀብት የሚሰበሰብበት መሆኑን ገልጸዋል።
አቶ ሺሰማ አክለውም የሚተከሉ ችግኞች ለህብረተሰቡ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ የሚሰጡ እንዲሁም የአፈርና ውሃ ጠበቃን የሚያስጠብቁ መሆናቸው አመላክተው ለዚህ ፕሮግራም መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት አመስግነዋል።
በመጨረሻሞ ለማህበረሰቡ በልማትና በመሰረተ ልማት ባለውለታ የሆኑ አካላት እውቅና የተሰጠ ሲሆን ቀጣይ 13ኛው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር በምስራቅ ጉራጌ ዞን በደቡብ ሶዶ ወረዳ የሚደረግ ይሆናል።