የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር (ጉልባማ) የሚያከናውነው አመታዊ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም የዞኑ ማህበረሰብ አንድነት ለማጠናከርና የዞኑን ገጽታ ለማስተዋወቅ እንደሚረዳ ተገለጸ።

በልማት ማህበሩ አዘጋጅነት 10ኛውን ዙር የጉዞ አረንጓዴ ልማት የችግኝ ተከላ ፕሮግራም በመስቃን ወረዳ ተካሄደ።

የልማት ማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ሺሰማ ገብረስላሴ ማህበሩ የጉራጌ ህዝብ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ለማሳደግና ባህላዊ እሴቶቹን ተጠብቀው እንዲቆዩ በዞኑና ከዞኑ ውጭ የሚኖሩ የዞኑ ተወላጆች እያስተባበረ ይገኛል ብለዋል።

የጉራጌ አንድነት ለማጠናከር “ጠንካራ አንድነት ለዘላቂ ልማት” በሚል መሪቃል በከተማና በገጠር፣ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገር እንዲሁም በተለያዩ ወረዳዎች የሚገኙ የብሄሩ ተወላጆች ግንኙነት እንዲጠናከር እያደረገው ያለውን ተግባር አበረታች እንደሆነም የቦርድ ሰብሳቢው ገልጸዋል።

በዘቢዳር ኢኒሼቲቭ የተጀመረው የችግኝ ተከላ የዘቢዳር ሰንሰለታማው ተራራ በእጽዋት ከመሸፈን ባለፈ ዞኑን ለማስተዋወቅና በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚገኙ የዞኑ ተወላጆች ግንኙነት ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።

እንደ አቶ ሺሰማ ገለፃ ባለፉት ዘጠኝ አመታት ከተተከሉ ችግኞች መካከል 85 በመቶ የሚሆኑትን ጸድቀዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል በበኩላቸው ጉዞ ወደ አረንጓዴ ልማት በአለም ብሎም በሀገራችን በተከሰተው የአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት የሚከሰቱ ተፈጥሯዊና ሰውሰራሽ አደጋዎች በመከላከል ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ለመገንባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።

ይህ የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማት ፕሮግራም ከዞኑ አልፎ በሀገሪቱ የመንግስት እና የህዝብ አጀንዳ በመሆን በጠቅላይ ሚኒስትሩ እየተመራ ይገኛል ብለዋል።

የአረንጓዴ አሻራ ከተጀመረ ወዲህ ልማት ማህበሩ ለችግኝ ተከላው ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሰራ እንደሚገኝ አቶ መሀመድ ገልጸዋል።

የአረንጓዴ ልማት ስራው የተራቆቱ አካባቢዎች እንዲያገግሙ፣ ዝርያቸው እየተመናመነ የሚገኙትን ሀገር በቀል ዛፎች እንዲጠበቁና የውሀ ሀብቶች እንዲጎለብቱ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከተ በመሆኑ የዞኑ አስተዳደር ለስራው አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አቶ መሀመድ ገልጸዋል።

ባለፉት አመታት በተሰራው የአረንጓዴ ልማት ስራና በሚደረጉ የእንክብካቤ ስራዎች እንደ ዞን የሚተከሉ ችግኞች ፅድቀት 84 በመቶ የደረሰ ሲሆን የዞኑ የደን ሽፋን በ2010 ዓ.ም ከነበረበት 18 በመቶ ወደ 24 ከመቶ መድረሱም ተናግረዋል።

በደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የኢኮኖሚ ዘርፍ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ፕላን ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ባዩሽ ተስፋዬ ችግኝ መትከል ለጥላ፣ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ፣ ለእንስሳት መኖ፣ ለአፈርና ውሀ ጥበቃ አገልግሎት ስለሚሰጥ የተተከሉ ችግኞች መንከባከብ ይገባል ብለዋል።

የመስቃን ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሀሰን ከድር እንደገለፁት በአስረኛው ዙር በ”ጉዞ አረንጓዴ ልማት ” በችግኝ ተከላ ተሳታፊዎች ከፍተኛ ጠቀሜታ ያላቸው እስከ 30 ሺ ችግኞች እንደሚተከሉ ገልጸዋል።

የወረዳው መንግስት የሚተከሉ ችግኞች እንዲፀድቁ ማህበረሰቡ በማስተባበር ተገቢ እንክብካቤ እንደሚደረግላቸውም አረጋግጠዋል።

በችግኝ ተከላ ወቅት ካነጋገርናቸው የዞኑ ተወላጆች መካከል ድምጻዊ ጸጋዬ ስሜ፣ አቶ ተስፋዬ ደምስ እና ወይዘሮ አስቴር ቢረዳ ይገኙበታል።

እንደ አስተያየት ሰጪዎቹ ገለጻ ጉልባማ በየአመቱ እያከናወነው ያለው የችግኝ ተከላ ፕሮግራም እርስ በርሳቸው እንዲተዋወቁ እና አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ አስችሏቸዋል።
የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ባህል ሆኖ መቀጠሉ የዞኑ ተወላጅ ባለሀብቶች መዋዕለ ንዋያቸውን እንዲያፈሱ ያደርገሰል ብለዋል።

በመሆኑም ይህን መሰል የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉና የተተከሉ ችግኞች እንዲጸድቁ ሁሉም ኃላፊነቱን ሊወጣ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በእለቱ የእድሜ ዘመን ተሸላሚዎች በተለይም ለትዝታው ንጉስ አርቱስት ማህሙድ አህመድ፣ ለአቶ ፍቃዱ አለመናገር እና ለሀጅ ገረሱ ዱኪ ባለፉት አመታት ለዞኑ ልማት፣ለሰላምና ኪነጥበብ ላደረጉት አስተዋጽኦ እውቅና እና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።

በመጨረሻም የ2015 የጉዞ አረንጓዴ ልማት አዘጋጅ የአበሽጌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ መላኩ ብርሃኔ ከመስቃን ወረዳ አቻቸው የችግኝ እርክብክብ አድርገዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ!
= የፈረሰውን እንገንባ!
= ለፈተና እንዘጋጅ!

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን ተጭነው ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን :-
Facebook:-https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub:- https://youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36CxQ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *