የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር (ጉልባማ) እያከናወናቸዉ ያሉና የጀመራቸዉን የልማት ስራዎች ተጠናቀዉ ለማህበረሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማድረግ ማህበሩ የገቢ ማስገኛ መንገዶች በመፍጠር፣ አባላት በማፍራትና ከተለያዩ ግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር ተቀናጅቶ መስራት እንዳለበት ተገለጸ።

የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር (ጉልባማ) አመታዊ ጠቅላላ ጉባኤዉን ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ አካሄዷል።

ማህበሩ እየተከናወኑ ያሉና የጀመራቸዉ የልማት ስራዎች ተጠናቀዉ ለማህበረሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ በከተማና በገጠር የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችና እያደረጉት ያለዉን ድጋፍ ማጠናከር ይገባል።

የጉራጌ ልማትና ባህል (ጉልባማ) የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሽሰማ ገብረስላሴ እንዳሉት የህዝብ ፣የመንግስትና የልማት አጋሮችን አቅሞች አስተባብሮ ማህበሩ ዉጤታማ ስራ መስራት አለበት ብለዋል።

ጅምር የልማት ስራዎችን ለማጠናቀቅ የሚያስችል የአባላትና የደጋፊዎች ንቅናቄ በመፍጠር ሀብት ማሰባሰብ እንደሚገባም ፣ ከልማት አጋሮች ጋር የተጀመሩ ግንኙነቶች አጠናክሮ ማስቀጠል፣ በገጠርና በከተማ የሚኖረዉን ማህበረሰብ እንዲሁም የልማት አጋሮችን በተገቢዉ ማስተባበር እንደሚገባም አሳስበዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ በበኩላቸዉ አቶ ላጫ ጋሩማ እንዳሉት የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር ሁለንተናዊ የልማት እንቅስቃሴዉ አጠናክሮ ለማስቀጠል ሁሉም የማህበረሰቡ ክፍሎች አባል ሆነዉ መደገፍ አለባቸዉ።

ማህበሩ ከ468 ሺህ በላይ አባላት ለማፍራት አቅዶ በዚህም 46 በመቶ የሚሆነዉ ብቻ ተፈጻሚ የሆነ ሲሆን ከአርሶአደር ጀምሮ በሀገር ዉስጥና በዉጭ ሀገር የሚገኙ ባለሀብቶች ፣ሙሁራን በሙሉ አባል በመሆንና የአባልነት መዋጮ በአመቱ እንዲያጠናቅቅ ማድረግ ይገባል ብለዋል።

ጉራጌ ተቆጥሮ የማያልቅ ባህላዊ እሴቶች ባለቤት ሲሆን ለኢትዮጵያ ብሎም ለአለም የሚሆኑ ትላልቅ ቅርሶች፣ ልዩ ባህሎችና ማንነት ያለዉ ህዝብ ሲሆን እነዚህም የማጉላት የማልማትና የማስተዋወቅ ስራ ላይ በስፋት መሰራት እንዳለበትም አስረድተዋል።

የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር (ጉልባማ) የጠቅላላ ጉባኤ ሰብሳቢ አቶ ኤልያስ ሼኩር እንዳሉት ማህበሩ በበርካታ አካባቢዎች የሰራቸዉ በርካታ የልማት ስራዎች ማበረታታት ይገባል።

በሀገሪቱ ለዉጡ ከመጣ በኋላ መልካም ጅማሮ ከሚባሉ ነገሮች አንዱ የተጀመሩ ልማቶች ጀምሮ መጨረስ ነዉ ብለዉ በቡታጅራ ከተማ እየተከናወነ ያለዉ የህንጻ ግንባታ ፣ በአዲስ አበባ ያለዉ የባህል ማዕከል ግንባታዎች ስኬታማ እንዲሆኑ በትኩረት መሰራት እንዳለበትም አመላክተዋል።

የጉራጌ ልማትና ባህል ማህበር (ጉልባማ ) ስራ አስኪያጅ አቶ ቅባቱ ተሰማ ለጉባኤዉ ታዳሚዎች ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት የቡታጅራ ሁለገብ ህንጻ ግንባታ የመጀመሪያ ወለል ግንባታ ስራ ሙሉ ለሙሉ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን የአንደኛ ፎቅና የዉሃ መከላከል ስራዎችን በማጠናቀቅ ፣ ለሁለት የሆቴልና ካፌ ፣ አንድ ጌም ዞን ፣ስምንት ለተለያዩ ንግድ ስራ የሚሆኑ ሱቆች ጨረታ ወጥቶላቸዉ አሸናፊዎች ተለይተዉ ስራ ጀምረዋል።

በዞኑ ዉስጥ በ14 ወረዳዎችና በ8 ከተማ አስተዳድሮች፣ ፣በዞን ማዕከል በ23 ጽህፈት ቤቶች በበጀት አመቱ 566 ተቋማት 448 ሺህ 663 የማህበረሰብ ክፍሎች አባላት ለማፍራትና 18 ሚሊየን 103 ሺህ 940 ብር መዋጮ ለመሰብሰብ ታቅዶ ዷዚህም በ208 ሺህ 125 አባላት በመመልመል 13 ሚሊየን 174ሺህ 166 ብር ከ58 ሳንቲም ማሰባሰብ መቻሉም ተናግረዋል።

ማህበሩ የጉራጌ ብሔረሰብ ችግሮችን ለመቅረፍ በበርካታ ዘርፎች ማህበረሰቡን የሚጠቅሙ የተለያዩ የልማት ስራዎች እያከናወነ መሆኑም ጠቁመዋል።

በጉባኤዉ የተገኙ አንዳንድ ባለድርሻ አካላት በሰጡት አስተያየት ማህበሩ የገቢ ማስገኛ መንገዶችን በመፍጠርና ከቸለያዩ ግብረሰናይ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት ለአካባቢዉ ልማት ዉጤታማ ሰራ መስራት ይኖርበታል።

የጉራጌ ባህላዊ ዳኝነት በአካባቢዉ የሚፈጠሩ ችግሮች በመቅረፍ ረገድ እየተሰራበት ያለዉን በጎ ስራ የበለጠ ማጠናከርና ባህላዊ የዳኝነት ስርአት በሰነድ ተሰንዶ ማስቀመጥ እንደሚገባም አመላክተዋል።

ተጀምረዉ ያልተጠናቀቁ የልማት ስራዎች በተገቢዉ እንዲጠናቀቁና ለታለመላቸዉ አላማ እንዲዉሉ ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል ሲል የዘገበዉ የጉራጌጨዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ነዉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *