የዳልጋ ከብቶችን ዝርያ በማሻሻል በእንስሳት ዘርፍ የአርሶ አደሩ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ትኩረት አድርጎ መሰራት እንዳለበት የጉራጌ ዞን ግብርና መምርያ አስታወቀ።


በጉራጌ ዞን አቀፍ የ2014 አመተ ምህረት የዳልጋ ከብቶችን በሆርሞን የማድራት ወይም የሲንክሮናይዜሽን ዘመቻ በእንድብር ከተማ አስተዳደር ዛሬ በይፋ ተጀምሯል።

የጉራጌ ዞን የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ መሀመድ ሙደሲር በመክፈቻው ላይ እንደገለጹት በዞኑ ከ2 ሚሊየን በላይ የቀንድ ከብቶች ቢኖሩም ዝርያቸው የተሻሻሉት ከብቶች ከመቶ ሺ እንደማይበልጥ ገልጸው ዞኑ በባለፉት አመታት የዝርያ ማሻሻል ተግባር ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት እንደሚገኝ አስታውቋል።

አቶ መሀመድ አክለውም የወተት ምርታማነትን ለማሳደግ እና የአርሶ አደሩ ኢኮኖሚ ለመጨመር በመደበኛ ማዳቀል ፣በሆርሞን ማድራት ቴክኖሎጂ እና በኮርማ የማዳቀል ዘዴዎች በመጠቀም እየተሰራበት እንደሆነም አመላክቷል።

ባለፈው አመት እንደ ዞን 22ሺ ከብቶች የተዳቀሉ ሲሆን ከነዚህም 90 በመቶ መሳካቱን የተናገሩት አቶ መሀመድ ሙደሲር በ2014 ዓመተ ምህረት በ17 ወረዳና በ8 ከተማ አስተዳደሮች በ22 ክላስተር እስከ ህዳር 23/2014 ዓ/ም 2ሺ 450 እንስሳቶች በሆርሞን የማድራት ስራ ይሰራል ብለዋል።

በዞኑ በአመቱ 92 ሺ ቶን የወተት ምርት የሚገኝ ሲሆን ይህን የወተት አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ ዝርያ ማሻሻሉ ላይ ትኩረት ተደርጎ እየተሰራበት ሲሆን የወተት ምርትና ምርታማነቱን እና የአርሶ አደሩ ኢኮኖሚ ለማሳደግ ዝርያ የማሻሻል ተግባሩ ላይ ትኩረት ተደርጎ መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል።

አቶ መሀመድ አክለውም በአሁን ወቅት ከፍተኛ የሆነ የመኖ ችግር እያጋጠመ በመሆኑ አርሶ አደሩ በጓሮው ቢያንስ 500 ካሬ መሬት መኖ እንዲተክል እየተደረገ እንደነበር አስታውሰዋል ።

66 ፐርሰንቱ የዞኑ የወጣቶች ስራ እድል እየተፈጠረበት ያለ የስራ ዘርፍ አንዱ እንደሆነ ያስታወሱት ኃላፊው ሁሉም ባለድርሻ አካል ትኩረት አድርጎ እንዲሰራበት አሳውቀዋል።

የጉራጌ ዞን ረዳት የመንግስት ተጠሪ አቶ አለማየሁ ገ/መስቀል የ2014 የሲንክሮናይዜሽን ዘመቻ በይፋ ባስጀመሩበት ወቅት እንዳሉት የዳልጋ ከብት በመደበኛ የማደቃል ስራው በየጊዜው እየተሰራ በመሆኑ የእንስሳት ዝርያዎች በማሻሻል ምርትና ምርታማነቱ እየጨመረ መምጣቱንና በየጊዜው የሚወለዱ ጥጆች ቁጥር በከፍተኛ መጨመሩን ተናግረዋል።

ዝርያ ማሻሻል ሲባል ከብቶችን በቁጥር ማሳደግ ሳይሆን በጥቂት ከብቶች ብዙ የወተት ምርት እንዲገኝ ማስቻል በመሆኑ ሁሉም ይህንን ተገንዝቦ መስራት እንደሚጠበቅበት መክረዋል።

ምርቱን ለመጨመር ለአርሶ አደሩ በቂ ግንዛቤ በመስጠት ፣ባለሙያ በማሰልጠን ፣መኖዎችን በማቅረብ እና የክትትልና ድጋፍ ስራ በማጠናከር ለተግባሩ ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል ሲሉ ገልጸዋል።

የወልቂጤ ግብርና ምርምር ኢኒስቲትዩት የእንስሳት ምርምር ስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ አቤል ሰብስቤ በበኩላቸው ዞኑ ለዝርያ ማሻሻሉ ተግባር ምቹ የአየር ሁኔታ ያለው ሲሆን ተቋሙም በወተት ምርታማነት ላይ በቂ የምርምርና ምርታማነቱ ላይ በትኩረት እየተሰራበት እንደሆነም አመላክተዋል።

በዝርያ ማሻሻል ተግባሩ ከልየታው ጀምሮ ጥጃው እስከሚወለድ ድረስ ሆርሞኑ እንዳይጨናገፍ ፣አመጋገባቸው እንዲያስተካክሉ ፣ጤናቸው የተጠበቀ እንዲሆንና አስፈላጊ የሆነ ክትትል የማድረግ ስራ እንደሚሰራ አመላክተው ቀጣይም በትኩረት ይሰራበታል ብለዋል።

የእንድብር ከተማ እንስሳትና አሳ ሀብት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጸጋዬ ስሜ እንዳሉት በዚህ ተግባር 150 ከብቶች ላይ ዝርያ የማሻሻል ስራ ለመስራት መታቀዱና ሁሉም ባለድርሻ አካላት በነቂስ እንዲሳተፍ በዘመቻ የመስራት ስራ ይሰራል ሲሉ አሳውቀዋል።

አርሶ አደር ሳህሌ በርታ፤አርሶ አደር ሀብቴ ምርደዊ እና ወ/ሪት ሙሉቀን ግርማ የእንድብር ከተማ ነዋሪዎች ሲሆኑ ከዚህ በፊት ባህላዊ የከብት እርባታ እየተጠቀሙ በወተት ምርት ምንም አዋጪ እንዳልነበር አስታውሰው ዘመናዊ ዝርያ ማሻሻል ተግባር ከጀመሩ ጊዜ ጀምሮ ግን 1ሊትር ብቻ የምናገኝ ከነበረበት አሁን ከ5 ሊትር በላይ ማግኘት እየቻልን ነው ሲሉ ገልፀዋል።

በዘርፉ ውጤታማ ለመሆን የመኖ እጥረት ችግር እየገጠመን ነው ያሉ አስተያየት ሰጪዎች የወተት ምርትና ምርታማነቱ ለማሳደግ በቀጣይ ዝርያ ማሻሻል ተግባሩ ላይ በትኩረት እንደሚሰሩበት ተናግረዋል ሲል የዘገበውየጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው ።

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *