የዞኑ ፍትህ መምሪያ ኃላፊ አቶ ኤልያስ ሰብለጋ የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ለማሻሻል መንግስት የ3 አመት የፍትህ ትራንስፎርሜሽን እቅድ በማዘጋጀት ወደ ተግባር የገባ ሲሆን ከፌደራል ጀምሮ በየደረጃው በሚገኙ የምክር ቤት አፈጉባኤዎች እየተመራ እንደሚገኝ አስገንዝበዋል።

መምሪያው የ2016 በጀት አመት የማጠቃለያ እቅድ አፈጻጸም በወልቂጤ ከተማ ገምግሟል።

እንደ አቶ ኤልያስ ገለጻ በፍትህ ትራንስፎርሜሽን ትኩረት ከተሰጣቸው አስር ዘርፎች መካከል አንዱ የሽምግልና ስርዓት ማጠናከር ሲሆን ህብረተሰቡ በአቅራቢያው ጉዳዩን እንዲፈታ ያስችለዋል።ለዚህም መምሪያው በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በበጀት አመቱ ከዞኑ ማህበረሰብ ያፈነገጡ ከባድ የግድያ ወንጀሎች የተፈጸሙ ሲሆን ወንጀለኞች ለፈፀሟቸው ድርጊቶች የፍርድ ውሳኔ ተሰጥቷቸዋል ብለዋል።

ወንጀለኞችን በህግ እንዲጠየቁ ከማድረግ ጎን ለጎን ወንጀልን አስቀድሞ ለመከላከል ከፖሊስ፣ ከአቃቤያነ ህግና ከፍርድቤቶች ጋር በቅንጅት እየተሰራ እንደሚገኝ አቶ ኤልያስ አስረድተዋል።

በዞኑ “ፍትህ በቀዬዋ ” በሚል መሪቃል ባለጉዳዮች በአቅራቢያቸው ፍትህ እንዲያገኙ እስከ ቀበሌ ድረስ በመውረድ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ መዋቅሮች ተሞክሮ በማስፋት ህብረተሰቡ በፍትህ ተቋማት ላይ ያለውን እምነት ማጎልበት እንደሚገባ ኃላፊው ገልጸዋል።

በግብር አሰባሰብ ላይ የሚስተዋሉ ችግሮች በመቅረፍ መንግስት ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ገቢ እንዲያገኝ እና የኦዲት ግኝት፣ የግብዓት እዳና ለስራ አጥ ወጣቶች የተሰታጨ ተዘዋዋሪ ፈንድ ለማስመለስ መስራት እንደሚገባ አቶ ኤልያስ ተናግረዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በበኩላቸው በ2016 በጀት አመት በፍትህ ተቋም የተመዘገበው አፈጻጸም አበረታች ቢሆንም በቀጣይ በዞኑ የሚፈጸሙ ቀላልና ከባድ ወንጀሎች አስቀድሞ ለመከላከል ባለድርሻ አካላት ተቀናጅተው ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።

መምሪያው የታችኛው መዋቅሮች ለማብቃት ድጋፍና ክትትል እያደረገ ሲሆን በበጀት አመቱ በጉድለት የተለዩ በየአካባቢው ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች እልባት እንዲሰጣቸው መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

የፍትህ ተቋማት ከዘር፣ ከሃይማኖት እና ከማንነት የጸዳ አገልግሎት ሊሰጡ ይገባል ያሉት ተሳታፊዎቹ በዞኑ የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥ ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ ፖሊስ፣ ፍርድ ቤት፣ አቃቤያነ ህግ ተቀናጅተው መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በዞኑ በበጀት አመቱ የተሻለ አፈጻጸም ያስመዘገቡ የእዣ፣ የቸሃ እና የምሁር አክሊል ወረዳ ፍትህ ጽ/ቤቶች ዋንጫና ሰርተፊኬት ተበርክቶላቸዋል።

በመድረኩ የወረዳና የከተማ አስተዳደር ፍትህ ጽ/ቤት ኃላፊዎች፣ ሲቪክ ማህበራት፣ የመምሪያው አቃቢያነ ህጎች፣ የየመምሪያ ተወካዮች፣ የዞኑ ከፍተኛ ወርድ ቤት ዳኛ፣ እና የኦሞ ባንክ ተወካይ ተሳትፈዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *