የዞኑ ስፖርታዊ እንቅስቃሴ ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ መላዉ ማህበረሰቡ ያሳተፈ የሀብት አሰባሰብ ላይ በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባም የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

የዞኑ ስፖርት ምክር ቤት 21ኛዉ ጠቅላላ ጉባኤዉን ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ ተካሄዷል።

የወልቂጤ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ለማጠናከር ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረዉ በማድረግ ከማህበረሰቡ ሀብት በተገቢዉ በማሰባሰብ ክለቡን ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ ይገባል።

በስፖርት ምክር ቤት ጉባኤዉ ላይ የተገኙት የጉራጌ ዞን ዋና አሰተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ እንዳሉት ዞኑ በስፖርታዊ እንቅስቃሴና ተሳትፎ ከበፊትም ጀምሮ ጠንካራ ፉክክርና ዉድድር በማድረግ ዉጤታማ እንደሆነ ይታወቃል።

ለስፖርት ተብሎ ከህዝብ የሚሰበሰበዉን ሀብት ለታለመለት አላማ በማዋል በዘርፉ የሚፈለገዉ ዉጤት እንዲመጣ አጽእኖት ተሰጥቶት መሰራት አለበት ብለዋል።

ጠንካራና ዉጤታማ ስፖርተኛ ለመፍጠር የትምህርት ቤቶች የዉስጥ ለዉስጥ ዉድድሮች በማካሄድ ተተኪ ስፖርተኞች ማፍራት እንደሚገባና ለዚህም ስኬት የአመራሩና የስፖርቱ ቤተሰብ ትልቁን ድርሻ ወስደዉ መስራት እንዳለባቸዉም አስታዉቀዋል።

ስፖርታዊ ዉድድሮች ከፍተኛ ሀብት የሚጠይቁ ሲሆን የሀብት አሰባሰቡ ላይ ከመቼዉም ጊዜ በላይ በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባም አመላክተዋል።

በሁሉም የስፖርት አይነቶች ዞኑ ዉጤታማና ስኬታማ እንዲሆን የሀብት አሰባሰብ ፣ የስፖርት ማዘዉተሪያ ስፍራ በማመቻቸት ወጣቶችን ተጠቃሚ ለማድረግ አመራሩ ከዘርፉ ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተዉ መስራት እንዳለባቸዉም አብራርተዋል።

የጉራጌ ዞን ወጣቶችና ስፖርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሄኖክ አብድልሰመድ እንዳሉት የወጣቶች ስብዕና ለመገንባት በስፖርት ማዘዉተሪያ ስፍራዎች ያሉ ችግሮች በተገቢዉ በመቅረፍ ወጣቶች ከሱስ ይልቅ የስፖርት ማዘዉተሪያ ስፍራዎች እንዲዉሉ ማድረግ እንደሚገባም አመላክተዋል።

የወልቂጤ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ለማጠናከር ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረዉ በማድረግ ከማህበረሰቡ ሀብት በተገቢዉ በማሰባሰብ ክለቡን ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ ይገባል ብለዋል።

የስፖርት ምክር ቤት ከተቋቋመበት ዓላማ አንፃር ወጣቱን ብሎም መላው የማህበረሰብ ክፍሎች በስፖርት ልማት፤ በማህበራዊና በኢኮኖሚ መስክ ተጠቃሚ ለማድረግ በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል ፡፡

ስፖርት ካለው ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አንፃር ህዝቡን በስፖርት ልማት የማቀራረብ፣ ያሉንን ባህላዊ እሴቶች እንዲጎለብቱ፣ ጤናማና አምራች ማህበረሰብ በመፍጠር፣ ካላስፈላጊ ጎጂ ልምዶች በመራቅ የልምድ ልውውጦች እንዲጠናከሩ እንዲሁም ታዳጊ ህፃናቶች ፣ ወጣቶች ብሎም መላው ማህበረሰብ በስፖርት ልማት ተጠቃሚነታቸው እየተረጋገጠ መጥቷል ብለዋል።

በዞኑ በመንግስትም ይሁን በግለሰቦች የተቋቋሙ ከ60 በላይ ፕሮጀክቶች የሚገኙ ሲሆን እነዚህ ፕሮጀክቶች ያላሰለሰ ድጋፍና ክትትል በማድረግ ህፃናት ብሎም ወጣቶች የዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በርካታ ስራዎች መሰራቱም አመላክተዋል።

የወልቂጤ ከተማ እግር ኳስ ክለብ፤ የወልቂጤ ከተማ ቅርጫት ኳስ ክለብ እና የዘቢዳር አትሌትክስ ክለቦች በሀገር አቀፍ ደረጃ በርካታ ውድድሮችን መሳተፍ የቻሉ ሲሆን የዞኑ መንግስትም የገንዘብ እና የቴክኒክ ድጋፎችን በስፋት በማድረግ ክለቦች ጥሩ ተፎካካሪ እንዲሆኑ ማድረግ የተቻለ እንደሆነም አብራርተዋል።

የጉራጌ ዞን ስፖርት መምሪያ የስፖርት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አደም ሽኩር የስፖርት ምክር ቤቱ ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት ስፖርት ከመንግስት ድጎማ ተላቆ ህዝባዊ መሰረት እንዲኖረዉ ለማድረግ አጽእኖት ተሰጥቶት መሰራት እንዳለበትም አብራርተዋል።

የስፖርት ምክር ቤት የፋይናንስ አሰራሩን ግልጽና ኦዲት እንዲያደርጉ የማድረጉም ስራ በትኩረት እየተሰራ እንደሆነም አመላክተዉ የስፖርት ማዘዉተሪያ ስፍራዎች በማዘጋጀት ጤነኛና አምራች ዜጋ ማፍራት እንደሚገባም ተናግረዋል።

የስፖርት ምክር ቤቱ በቀረበዉ የማሻሻያ ሰነድ ላይ ተወያይቶ በቀጣይ በአርሰአደሩ ከነጋዴዉ ከመንግስት ሰራተኛዉ ከባለሀብቱና ከመላዉ ማህበረሰብ ለሚደረገዉ የሀብት አሰባሰብ በሙሉ ድምጽ ማጽደቁም አስረድተዋል።

በጉባኤዉ የተገኙ አንዳንድ ባለድርሻ አካላቶች በሰጡት አስተያየት የክለቦች ሰፖርታዊ እንቅስቃሴ በእዉቀትና ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በመምራት ክለቦችን ዉጤታማና የተሻለ ደረጃ ማድረስ ይገባል።

የወልቂጤ ከተማ ቅርጫት ኳስ ሰፖርት እየፈረሰ ያለበት ሁኔታ ላይ መድረሱም አንስተዉ ክለቡ በሀገር ደረጃ አካባቢዉን እያስተዋወቀ ያለ ክለብ በመሆኑም ክለቡ እንዳይፈርስ ትኩረት ሊሰጠዉ እንደሚገባም አመላክተዋል።

የስፖርት ማዘዉተሪያ ስፍራዎች አካባቢ ያሉ ችግሮች ትኩረት አድርጎ መስራት እንዲሁም የሚሰበሰቡ ሀብቶች በተገቢዉ ለተለመለት አላማ እንዲዉል የቁጥጥር ስራዉ ትኩረት ተደርጎ ሊሰራበትም እንደሚገባም አመላክተዋል።

ታዳጊዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ በመስራት የተሻለ ዉጤት ማምጣትና ተተኪ ስፖርተኞች በብዛት ለማፍራት ባለድርሻ አካላቶች ከመቼዉም ጊዜ በላይ ተቀናጅተዉ መስራት አንዳለባቸዉም አስረድተዋል።

በመጨረሻም በጉባኤዉ ለተለያዩ የስፖርት ፌዴሬሽኖች፣ ለዳኞች፣ ለወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ፣ ለዞኑ ቀይ መስቀል ቅርንጫፍና ለወልቂጤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ እንዲሁም ለሁሉም ከተማ አስተዳደሮችና ወረዳዎች የስፖርት ምክር ቤቶች የሰርተፍኬት ሽልማት ተበርክቶላቸዋል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *