በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ በአምበሊ ቀበሌ በህብረተሰብና በመንግስት ትብብር የተገነባው 20 ኪሎሜትር አዲስና ነባር የመንገድ ጥገና የጠጠር መንገድ ተመረቆ ለትራፊክ ክፍት ሆነ።
የኢፌድሪ ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር መኩሪያ ኃይሌ የጉራጌ ባለሀብቶች የቀድሞ አባቶቹ አሻራ በማስቀጠል ላይ እንደሚገኙ ያነሱት ኮሚሽነሩ ወጣቱ ትውልድም ይህ ተግባር ሊያስቀጥሉ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በርካታ ኢንቨስትመንት ፈሶበት የተገነባው መንገዱ ለረዥም አመታት አገልግሎት መስጠት እንዲችል ህብረተሰቡ በተለያዩ መንገድ መንከባከብና መጠበቅ እንዳለባቸው አንስተዋል።
የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ የመንገድ ሁለንተናዊ ጥቅም አስቀድሞ የተረዱት የቀድሞ አባቶች ያከናወኑት አርአያነት ያለው ተግባር አሁን ላይ የዞኑ ባለሀብቶች ተግባሩ እያስቀጠሉት ይገኛሉ።
የመንግስት አቅም ውስን ነው ያሉት አቶ ላጫ በተጠናቀቀው በጀት አመት የዞኑ ማህበረሰብ የቀድሞ የአባቶቹን አርአያ በመከተል በመንገድና በትምህርት መሰረተ ልማት ላይ እያደረጉት ያለው አበረታች እንቅስቃሴ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ተናግረዋል።
አካባቢው ወጣ ገባ ከመሆኑ አንጻር መንገዱ ለረጅም አመት ማገልገል እንዲችል ሁሉም በመቀናጀት መጠበቅ እንዳለበት አስገንዝበዋል።
በዞኑ አብዛኛው ትምህርት ቤቶች ከደረጃ በታች ናቸው ያሉት አቶ ላጫ በእዣ ወረዳ የአምበሊ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ደረጃ ለማሻሻልና የመምህራን መኖሪያ ለመገንባት የተጀመረው ስራ በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ ሁሉም ርብርብ ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል።
የጉራጌ ዞን ትራንስፖርትና መንገድ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ መራድ ከድር በተጠናቀቀው በጀት አመት 2መቶ77 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ሀብት በማሰባሰብ 2መቶ 98 ኪሎሜትር መንገድ ተሰርቷል።
ከዚህም 2መቶ 43 ኪሎሜትር ጠጠር የማልበስና ከ104 በላይ የተለያዩ ስትራክቸሮች፣ ድልድዮች፣ ፎርዶችና ቱቦዎች በመስራት ለትራፊክ ክፍት ማድረግ መቻሉንም ገልጸዋል።
በዞኑ ማህበረሰቡ በማስተባበር በመንገድ ልማት ስራ አበረታች ስራ መሰራቱን ያነሱት ኃላፊው በዚህ ክረምት ወቅትም ከፍተኛ አካባቢዎች ላይ ማህበረሰቡ በማስተባበር መንገዶችን ጥገና የማድረግ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የእዣ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዘውዱ ዱላ የመንገዱ መገንባት የአካባቢው አርሶ አደሮች ያመረቱትን ምርት ወደ ገበያ ከማውጣት ባለፈ እናቶች በጤና ተቋማት እንዲወልዱ በማድረግ የእናቶችና ህጻናት ሞት በመቀነስ ረገድ ፋይዳው ትልቅ ነው።
ልማት ማህበሩ የአምበሊ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ደረጃውን ለማሻሻልና የመምህራን የመኖሪያ ቤት ለመገንባት መሰረት ድንጋይ መቀመጡን ገልጸው የተጀመሩ የልማት ስራዎችን በጊዜና በጥራት እንዲጠናቀቁ ርብርብ ማድረግ ይገባል ብለዋል።
የአካባቢው የልማት ማህበር ኮሚቴ አስተባባሪ አትሌት ተሰማ አብሽሮ ልማት ማህበሩ የአካባቢው ማህበረሰብ እንግልት ለመቀነስ መንግስት ተደራሽ ያልሆነባቸውን መሰረተ ልማት ለማሟላት ማህበረሰቡ የመብራትና የንጹህ መጠጥ ውሃ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል።
ከዚህም ባለፈ ከ21 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የአካባቢው ነዋሪዎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚ ለማድረግ 13ነጥብ 5 ኪ.ሜ አዲስና 6ነጥብ 5 ኪ.ሜ ጥገና በማድረግ መንገዱ ተመርቆ ለትራፊክ ክፍት መሆኑንም አስረድተዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት ከዚህ ቀደም በአካባቢው መንገድ ባለመኖሩ ያመረቱት ምርት ወደ ገበያ ለማውጣት ከመቸገራቸውም ባለፈ እናቶች ወደ ጤና ተቋማት በቃሬዛ እንዲወሰዱ ይገደዱ እንደነበር አስታውሰዋል።
አሁን ላይ መንገዱ በመገንባቱ ችግሮቹ ተቀርፈው በሁሉም ዘርፎች ሁለንተናዊ ተጠቃሚ በመሆናቸው መደሰታቸውን ገልጸው የተገነባው መንገድ እንደሚጠብቁት አመላክተዋል።