የዞኑ ህዝብ የሚያነሳቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ለመፍታት በትኩረት እንዲሰራ የጉራጌ ዞን የፓርላማ እና የክልል ምክር ቤት አባላት አስታወቁ።


የጉራጌ ዞን የፓርላማ እና የክልል ምክር ቤት አባላት በየምርጫ ክልላቸው ከህዝቡ ጋር ሲያደርጉት የነበረ የውይይት መድረክ ማጠቃለያ በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።

የፓርላማ እና የክልል ምክር ቤት አባላት ከህብረተሰቡ የተሰጣቸው ሀሳብ ባቀረቡበት ወቅት እንዳሉት የዞኑ ማህበረሰብ ከመንግስት ጎን በመሆን በርካታ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን መንግስት በከፋ ችግር ውስጥ ሆኖ እያከናወናቸው ያሉ ስራዎች አበረታች ናቸው ብለዋል።

ሆኖም ግን የመብራት መቆራረጥና ተደራሽነት በዞኑ ማህበረሰብ ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር እያጋለጠው በመሆኑ የመብራት ዲስትሪክት በዞኑ እንዲኖር እንዲሁም የትምህርት ጥራትና የመምህራን ችግር ለመቅረፍ የመምህራን ኮሌጅ ሊኖር ይገባል ብለዋል።

በዞኑ በቂ የሆነ የሆስፒታል፣የጤና ጣበያ ተደራሽነት አለመኖርና በጤና ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ችግር እየተስተዋለ በመሆኑ በዘርፉ የሚታዩ ችግሮች ማረም ይገባል ያሉ ሲሆን በዞን፣በክልል፣በፌደራልና በተራዶ ድርጅቶች የተያዙ የካፒታል ፕሮጀከት ስራዎች መቀዛቀዛቸው አመላክተዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና መቀመጫ በወልቂጤ ከተማ የሚታየው የወሰን ጣልቃ ገብነት ችግር በአፋጣኝ ምላሽ አለመስጠቱ መላው የዞኑ ማህበረሰብ ለቅሬታ እየዳረገ በመሆኑ መንግስት ለከተማዋ እድገትና ሰላም በትኩረት መስራት እንዳለበት በትኩረት መነሳቱ ያስታወቁት አባላቶቹ ከአጎራባች ወረዳና ዞኖች ጋር የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮች ለህብረተሰቡ ስጋት እየሆኑ በመሆኑ መፍትሄ እንዲሰጠው ጠይቀዋል።

ህብረተሰቡ ከመንግስት ጋር በመሆን በርካታ መንገዶች የሚሰራ ቢሆንም መንግስት በዞኑ የአስፋልት ተደራሽነት ለማስፋት ቃል የተገቡ የመንገድ፣የንጹህ መጠጥ ውሃ የመስኖ፣የትምህርትና የተለያዩ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶች እንዲሰራ ተጠይቋል።

የማዳበርያ፣የምርጥ ዘር ችግር እና በቡና እንዲሁም በእንሰት አጠውልግ በሽታ እየተስፋፋ በመሆኑ መፍትሄ እንዲያገኝ መስራት እንደሚገባ መነሳቱ አብራርተዋል።

በዞኑ ህዝቡ የሚያነሳቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ መፍታት እንደሚገባ አባላቶቹ ተናግሯል።

የጉራጌ ዞን ዋና አፈ ጉባኤ ክብርት ወ/ሮ ልክነሽ ስርግማ እንደተናገሩት በዞን፣በክልልና በፌደራል መንግግት የሚሰሩ የካፒታል ፕሮጀክት ስራዎች በወቅቱ እንዲጠናቀቁና ከዞኑ አቅም በላይ የሆኑ ጉዳዮች ተፈጻሚ እንዲሆኑ የምክር ቤት አባላት ሚናቸው ከፍተኛ ነው ብለዋል።

የዞኑ ሰላምና ጸጥታ እንዳይረጋጋ የሚያደርጉ አካላት በመለየት የህግ የበላይነት እንዲረገጥ መስራት ያስፈልጋል ያሉት ክብርት ልክነሽ በየጊዜው በሚዘጋጁ መድረኮች ላይ የሚነሱ የህዝብ ጥያቄዎች ለህብረተሰቡ ተጨባጭ ምላሽ ለመስጠት ከመቼውም በላይ መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ እንደተናገሩት መንግስት ያልደረሰባቸው የልማት ስራዎች እንዲሰሩ ባለሀብቱ፣ህብረተሰቡና መንግስት እየሰሩት ያለው ስራ አጠናከሮ ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

የግብርና ዘርፉን ለማጠናከር ዘመናዊ የቴክኖሎጂ ቁሳቁሶች ዩኒየኖችን በማቀናጀት ይሰራል ያሉ ሲሆን የእንሰት አጠውልግና የቡና ግንድ አድርቅ በሽታ ለመቆጣጠር የምርመር ስራዎችን ላይ በአጽኖኦት የሰራል ነው ያሉት።

በዞኑ የመብራት ዲስትሪክት አለመኖሩ ከፍተኛ የሆነ የመብራት መቆራረጥና ተደራሽነት ችግር እየተስተዋለ በመሆኑ በዞኑ የመብራት ዲስትሪክት እንዲኖር የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በትምህርት በጤና፣በመንገድ፣በውሃ፣በሰላምና ጸጥታ እና በሌሎች ዘርፍ የሚከናወኑ ስራዎችን በማጠናከር የሚስተዋሉ ችግሮች ደረጃ በደረጃ ለመቅረፍ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግሯል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *