የወልቂጤ እግር ኳስ ስፖርት ክለብ ህዝባዊ መሰረት በማስያዝ ክለቡ በሀገርና በአለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን በሚደረገው ጥረት ሁሉም የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግ ተጠየቀ።


የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ እንዳለ ስጦታው የወልቂጤ ከነማ እግር ኳስ ክለብ ህዝባዊ መሰረት ለማስያዝ ብሎም ያለበትን የፋይናንስ እጥረት በዘላቂነት ለመቅረፍ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

አቶ እንዳለ ስጦታው በመግለጫቸውም የወልቂጤ እግር ኳስ ስፖርት ክለብ በ2012 ዓ.ም ወደ ፕሪምየር ሊግ ከተቀላቀለ ጊዜ ጀምሮ በተለያየ ምክንያት ህዝባዊ መሰረት ሳይዝ ቆይቷል።

ከዚህ በፊት ስፖርት ክለቡ በመንግስት ሀብት የሚመራ እንደነበር ጠቅሰው ህብረተሰቡ የሚጠይቃቸው በርካታ የመሰረተ ልማት ጥያቄ መኖሩን ተከትሎ ስፖርት ክለቡ ህዝባዊ መሰረት በማስያዝ ስፖርቱና ልማቱ ጎን ለጎን ማሳለጥ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።

ለዚህም ክለቡ ህዝባዊ መሰረት ለማስያዝ የፊታችን ሰኞ በቀን 27/2016 ዓ.ም ተወላጅ ባለሀብቶች፣ በሀገርና በአለም አቀፍ የሚኖሩ ባለሀብቶችን በማስተባበር የሀብት አሰባሰብ ስራ በስካላይት ሆቴል በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር የሚመራ መድረክ ተዘጋጅቷል።

በዚህም መድረክ ጥሪ የተደረገላቸው ሚኒስቴሮች፣ ባለሀብቶች፣ ተወላጅ ባለሀብቶች እና መላው የስፖርቱ ደጋፊ ማህበረሰብ የሚችሉትን አስተዋጽኦ በማድረግ ክለቡ ከገጠመው የፋይናንሺያል እጥረት ችግር ለማላቀቅ እንዲቻል ታስቦ የተዘጋጀ እንደሆነም አቶ እንዳለ አንስተዋል።

በሀብት ማሰባሰብ ስራውም ከ250 በላይ ባለሀብቶች እንደሚገኙ የጠቀሱት ከንቲባው በዚህም ከ60 እስከ 80 ሚሊዮን ብር ይሰበሰባል ተብሎ እንደታቀደም በመግለጽ።

የማህበረሰቡ አርማ የሆነው የወልቂጤ እግር ኳስ ስፖርት ክለብ አሁን ላይ ያለበትን ፋይናንሺያል እጥረት በዘላቂነት በመፍታት ዘላቂ የሆነ የገቢ አማራጮችን በመጠቀም ክለቡ ህዝባዊ ቅቡልነት እንዲኖረው በማድረግ በሀገርና በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማስቻል ነው።

መንግስት ያለውን ውስን ሀብት በመጠቀም ስፖርቱና ልማት ጎን ለጎን ለማሳለጥ ክለቡ ህዝባዊ መሰረት ለማስያዝ በሚደረገው ጥረት ባለሀብቱ፣ የንግዱ ማህበረሰብ፣ ነዋሪውና ሲቪል ሰርቫንቱ የበኩሉን አስተዋጽኦ እንዲያደርግም ጠይቀዋል።

ከዚህም ባለፈ የወልቂጤ እግር ኳስ ስፖርት ክለብ ብቻ ሳይሆን የዘቢዳር አትሌቲክስ ክለብ፣ ቅርጫት ኳስ እና በተለያየ መልኩ የተደራጁ ታዳጊ ስፖርት ቡድኖች ሁሉ ከመንግስት ሀብት የሚፈልጉ በመሆናቸው እነዚህን በስፖርት ጽህፈት ቤት ተደራጅተው ህዝባዊ መሰረት እንዲኖራቸው በማድረግ መንግስት ከሚመድበው ውስን በጀት ባለፈ ዘላቂ በሆነ መልኩ ስፖርቱ መምራት እንዲቻል በተለያዩ አማራጮች ገቢ የማሰባሰብ ስራ ለመስራት ታቅዷል።

በመሆኑም ይህ እንዲሳካ ሁሉም የንግዱ ማህበረሰብ፣ በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚኖሩ የክለቡ ደጋፊና ወዳጆች ተሳትፎ እንዲያደርጉም አቶ እንዳለ አሳስበዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *