የክርስቶስ ልደት በዓል ቀን ለምን ተለያየ?
“የጎርጎሮሳውያን የዘመን አቆጣጠር ያመጣው ፍልሰት”
የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን የዘመን አቆጣጠር ከአውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር የተለየ ነው።
አንደኛ ሰባት ዓመት ከስምንት ወር ከአስር ቀን ልዩነት አለ። ሁለተኛ እያንዳንዱ ወር የሚይዛቸው ቀናት ልዩነት አላቸው። ”በእያንዳንዱ ወር ውስጥ ከስድስት እስከ አስር ቀናት የሚደርሱ ልዩነቶች አሉ” ይላሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን የዘመን ቀመር (ባህረ ሃሳብ) ዙሪያ መጽሃፍ ያሳተሙት መጋቤ ጥበብ በእምነት ምትኩ ።
“የጎርጎሮሳውያኑ የዘመን አቆጣጠር እስከተጀመረበት ድረስ መላው ዓለም ተመሳሳይ የዘመን አቆጣጠር እንደነበረው ይታመናል “የሚሉት መጋቤ ጥበብ በእምነት” ነገር ግን በ1382 ዓ.ም የካቶሊክ ቤተክርስትያን ጳጳስ የነበረው ጎርጎሪዮስ የዘመን አቆጣጠሩ ችግር አለበት በሚል እንደገና እንዲሰላ ወሰነ። ከዚያም በአንድ ዓመት ውስጥ 365 ቀን ከ6 ሰዓት ነው ያለው የሚለውን ሃሳብ በማንሳት በየዓመቱ አንድ አንድ ሰዓት ተጨምሮብናል” ይላሉ።
ስለዚህ እንደ መጋቤ ጥበብ በእምነት ይህ አንድ ሰዓት ተጠራቅሞ መጨመር አለበት በማለት ከኒቂያ ጉባኤ ጀምሮ ያለውን አስልቶ በማሳሰብ 10 ቀን በመሙላቱ ኦክቶበር 5 የነበረውን ኦክቶበር 15 ነው ሲል አውጇል።
“ስለዚህ በእኛና በእነሱ መካከል እየቀነሰ የሚሄድ ቢሆንም የ10 ቀን ያህል ልዩነት አለን።”
እንግዲህ የኢትዮጵያ ቤተክርስትያን ከኖህ ዘመን ጀምሮ የነበራትን የቀን አቆጣጠር ጠብቃ ይዛ የቀጠለችና ምንም ነገር ያላሻሻለች በመሆኑ የነበረው እንዳለ ነው ሲሉ ያስረዳሉ።
በመሆኑም የአውሮፓውያንን የጊዜ ቀመር በሚከተሉ ሃገራት የክርስቶስ ልደት ዲሴምበር 25 (ታህሳስ 16) ይከበራል። ኢትዮጵያዊንን ጨምሮ ከ10 በላይ ሃገራት ደግሞ ከ12 ቀናት በኋላ ታህሳስ 29 ያከብራሉ።
የክርስቶስ ልደት በዓል ከሃይማኖታዊነቱ ስርዓት ጎን ለጎን የተለያዩ ባህላዊ ክንውኖች የሚካሄድበት
ነው፡፡ ለአብነት በመላዉ ሀገራችን የልጆች የገና ጫወታ እና በአዲስ አበባ ጃንሜዳ የሚካሄደው የፈረስ ጉግስ ጨዋታም ተያይዞ ይነሳል፡፡ በዚህ በዓል ከሌሎች በዓሎች በተለየ ስጦታ የመለዋወጥና የገና ዛፍ በመቁረጥና በማስዋብ የሚከበር ነው፡፡
በተለይም ጓደኛሞች፣ ፍቅረኞዎች እና የዩኒቨርሲቲና የኮሌጅ ተማሪዎች ፖስት ካርድ፣ ጌጣ ጌጥ፣ ሻማ፣ የእስኪርቢቶ ማስቀመጫና ሌላም ነገሮች አቅም በሚፈቅደውን ገዝተዉ ስጦታ የመለዋወጥ ባህል እንዳለ የተለያዩ መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
በዚህም በኢትዮጵያ ይሁን በሌሎች አገሮች ያሉ የገፀ በረከት መደብሮች ገበያ ከሚደራበት ወቅት አንዱ የልደት በዓል ነው፡፡
የገና ባህላዊ ጨዋታ
በበጋ ወቅት በአብዛኛው የኢትዮጵያ ክፍል የእረፍት ወቅት ነው። በእንዲህ አይነቱ የእረፍት ወቅት ደግሞ ጥምቀት፣ ሰርግና ሌሎች ጉዳዮች ይበዛሉ። እነዚህ ወቅቶች የጨዋታና የደስታ ናቸው። ወጣቶችና ልጅአገረዶች የደስታ ጊዜያቸው ነው። አዋቂዎችም ቢሆን ከሌሎች ወቅቶች በተለየ የሚጫወቱት በዚህ በበጋ ወቅት ነው። በበልግ እና በክረምት ወራት ሰርግ ወይም ሌላ ጉዳይ ቢኖር እንኳን ሰፊ ጊዜ ሰጥቶ ዘና የሚባልበት አይደለም። ቢያንጎራጉሩም በሥራ ቦታ ላይ ሆነው ነው። በዚህ በገና ሰሞን የበጋ ወቅት ግን ጎረቤት ከጎረቤት እየተጠራሩ ጨዋታው ይደምቃል፣ ሃሴቱ ይበዛል።
‹‹በገና ጨዋታ አይቆጡም ጌታ›› የተባለው ደግሞ ለልጆች ነው። የገና ወቅት የበጋ ወቅት ነው። በዚህ ወቅት ልጆች የሥራ ጫና የለባቸውም። የግብርና ሥራ አይታዘዙም፤ ከብትከብትም አይጠብቁም። በዚህ ወቅት ሰብል ስለሚሰበሰብ ከብቶች ከቤት ይመገባሉ ልጆችም ከብቶችን ጠብቁ ተብለው አይገደዱም።
ስለዚህ ልጆቹ ገና ሲጫወቱ ቤተሰብ ተቆጣኝ አልተቆጣኝ ብለው ሳይሆን በሙሉ ነፃነት ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ለነቐ ፣ ለኩርፍወ እና ለአሸንዳ በዓል ለልጆች እንደሚሰጠው ነፃነት በገና ጨዋታም ለልጆች ነፃነት ይሰጣቸዋል።
የገና ጨዋታ በበጋ ወቅት መሆኑ ወሩን ሙሉ ነፃነት ስለሚሰጣቸው እንጂ ለበዓሉ ዕለት ብቻ ከሆነ በክረምት ወራትም የተወሰነ ነጻነት አለ። ለምሳሌ ለፍልሰታ (ነሐሴ 16) እና ለእንቁጣጣሽ ልጆች እንዲጫወቱ ተብሎ ለእዚያን ቀን አባቶች ናቸው ከብት የሚጠብቁት። አባቶች እንኳን ባይመቻቸው ሌላ በጎልማሳነት ዕድሜ ላይ ያለ (ወደ ጨዋታው የማይሄድ) ሰው ከብት ይጠብቃል እንጂ ልጆች ከብት እንዲጠብቁ አይገደዱም። ወደ ገናችን እንመለስ።
የገና ጨዋታ ብዙ የተባለለት ነው። አሁን ላይ ከገጠር ይልቅ ወደ ከተማ ያዘነበለም ይመስላል (በእርግጥ ብዙ ባህሎች ከገጠር ይልቅ ወደ ከተማ እየገቡ ናቸው )። የገና ጨዋታ ከባህል ስፖርቶች አንዱ ሆኖም እውቅና ተሰጥቶታል። የገና ጨዋታ ራሱን ችሎ የመገናኛ ብዙኃን የዜና ሽፋን ለመሆን በቅቷል። ጨዋታውም የራሱ የሆነ ህግና ደንብ ያለው ነው። የራሱ የሆነ ጥበብ አለው።
እንደጉራጌ ዞን በአንዳንድ አካባቢዎቸ ለገና ጨዋታ የሚሰጡት ትኩረት ከፍተኛ እንደሞሆኑ መጠን ከዋነው የገና በዓል ከመድረሱ አንድ ወር በፊት ልጆች በቃንጫ ወይም በእንጨት ሩር (ቁየ) በማዘጋጀት ማታ ማታ ይጫወታሉ፡፡
ሌላው የገና ጨዋታ ጥበብ አዳጊዎች (ልጆች) ሲጫወቱ እርስ በርስ የሚለዋወጡት የቃል ግጥም ነው። ይወዳደሳሉ ይተራረባሉ። በተለይም በጨዋታው የተሸነፈው ቡድን በአሸናፊዎች ይተረባል፤ አሸናፊዎች ደግሞ የድል መልዕክት ባላቸው ስንኞች ይጫወታሉ። መጪውን የገና በዓል ምክንያት በማድረግ ስለገና ጨዋታ አንዳንድ እንበል። የገና ጨዋታ ሁለት ቡድኖች ጎራ ለይተው የሚጋጠሙበት ልዩ ባህላዊ ትዕይንት ነው። ቡድኖቹ አካባቢ ተለይቶ ወይም በምርጫ ሊመሰረት ይችላል፡፡
አንደኛው ቡድን ከቀኝ ወደ ግራ ከያዘ፣ ሌላኛው ቡድን ደግሞ ከግራ ወደ ቀኝ ያለውን ስፍራ ይይዛል። አቅጣጫውን ያልለየ ተጫዋች ካለ፣ ‹‹ሚናህን ለይ›› ወይም በጊላኸ ተብሎ፣ ካስፈለገም በዱላ ቸብ ተደርጎ፣ ቦታውን ይይዛል። በጨዋታ መሃል ሚናውን ስቶ በሌሎች ሚና በኩል ከተገኘ በጊላኸ ወይም ‹‹በሚናህ!›› የሚል ማስጠንቀቂያ ይሰጠዋል።
ልጆች ‹‹ሩሯን›› በጉራጊኛ ደግሞ ቁየ የሚመቱበት የዱላው ራስ ‹‹ገና›› ይባላል። ከወደ ራሱ እንደ ከዘራ ቆልመም ያለ ዱላ ነው።
እንደ ጉራጌ ብሔር ልጆች የገና በዓል ዋዜማ እለት ስለት በገባላቸው ቤት ሄደው የተዘጋጀላቸው ድግስ እየበሉ እየጠጡ አድረው በዋናው የገና በዓል እለት ተያይዘው ወደ ጨዋታቸው የሚጉበት ሁኔታ ነበር፡፡ አሁን አሁ እየተቀዛቀዘ የመጣ ቢሆንም፡፡
የገና ጨዋታ በዘመናዊ መልኩ በከተሞች ከምናየው ይለያል። በስፖርታዊ ውድድር ውስጥ በገባው ዘመናዊ የገና ጨዋታ ህግ መሰረት፤ ዱላውን (ገናውን ወይም ድቤው) ወደ ላይ ማንሳት አይቻልም። በጥንታዊው ወይም በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በሚደረገው የገና ጨዋታ ላይ ግን እንደተፈለገው በማንሳት፣ ሩሯን (ቁየው) አክርሮ መለጋት ይቻላል። ሌላው ደግሞ በዘመናዊው የገና ጨዋታ ስፖርት፣ ሩሯ የምትገባበት ሥፍራ እንደ እግር ኳስ የግብ ሥፍራ ያለው ነው። በጥንታዊው ጨዋታ ግን የገና ጨዋታው የሚካሄድበት ሜዳ ጫፎች የግብ ወይም የመልሚያ ቦታዎች ናቸው። ከሜዳው የተነሳም ተጫዋቾቹ እንደ ልባቸው እየሮጡ ይጫወታሉ። ጨዋታው በውጤት አሊያም በሽንፈት እየታጀበ ይቀጥላል። አንዱ ቡድን ሩሯን (ቁየ) እንዳገባ በተቃራኒው ቡድን ላይ የተረባ መዓት ይዥጎደጎዳል።
በገና ጨዋታ ላይ የሚሰነዘሩ ተረቦች ታዲያ እንደ መዝናኛና እንደ ማድመቂያ ነው የሚቆጥሩት።
የሚተርበው ቡድን እንኳን በተረቡ ይዝናናል ይስቃል እንጂ ቂም መያዝ ብሎ ነገር በገና ጨዋታ አይታሰብም። አጋጣሚ ቢመታም እንኳን፡፡
በጨዋታው ላይ የሚሰነዘሩ ወይም የሚወረወሩ ተረቦች በአብዛኛው በአካላዊ ገፅታ ላይ የተመሰረቱ ናቸው። ለምሳሌ ቁመት፣ እርዝመትና እጥረት፣ ውፍረትና ቅጥነት ወዘተ…
‹‹አሲና በል አሲና ገናዬ
እያሃ … አሲና ገናዬ››… እያሉ ተጋጣሚዎች ጨዋታውን ያደሩታል።
በጉራጊኛው ደግሞ
ያሆ ያሆ ለበሞ ሶርቴ ለበሞ
ይና ያበቾ
እንጭም በርቾ
ሳምር ትፍቾ ያሆ ያሆ ለበሞ ሶርቴ ለበሞ
የገና ጌተረ
ትንክየ ሰበረም ያሆ ያሆ ለበሞ ሶርቴ ለበሞ
…… እያሉ ይጫወታሉ፡፡
በመጨረሻም ቀን ሙሉ የገና ቸዋታቸውን ተጫውተው አመሻሽ ላይ ለመጪው አመት የሚደግስላቸው እማወራና አባወራ ተነጋግረዉ በተለይም ወንድ ልጅ ያልወለዱ ስለት የሚገባላቸው መርጠው ካበቁ በኃላ ሁላቸውም በጋራ ተሰብስበው እየጨፈሩ በመሄድ ገናቸውን (ድቤ) ቤታቸዉ በር ላይ በመጣል ቃል እንዲገቡ በማድረግ ላመቱ ያገናኘን ብለው ተመራርቀው ይለያያሉ፡፡ እንኳን ለ2014 ዓ/ም ለኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በዓል በሰላም አደረሳችሁ፡፡