የኪነ ጥበብ ዘርፉ በማልማትና በማሳደግ የዞኑ ብሔረሰብ እሴቶችን ይበልጥ ለማስተዋወቅ በትኩረት እንደሚሰራ የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

የዞኑ ብሔረሰብ እምቅ ሀብቶችን ለማልማትና ማህበራዊ ጥቅም ላይ ለማዋል በኪነ ጥበብ ዘርፉ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ገለፀ።

መምሪያው በተለያዩ የኪነ ጥበብ ዘርፍ ሲያሰለጥናቸው የቆየውን የዞኑ የባህል ኪነት ቡድን እና ባለተሰጥኦ አማተር የኪነ ጥበብ ከያንያን ስልጠና ተጠናቆ ዛሬ በወልቂጤ ከተማ በዞኑ ባህል አዳራሽ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት አስመረቀ።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይ ተገኝተው እንደገለፁት የዞኑ ብሔረሰብ እሴቶችን በማልማትና ለታዳሚያን በጥበብ መንገድ ተደራሽ ለማድረግ ለዞኑ ነባር የባህል ኪነት ቡድን አባላትና በዞኑ በሁሉም አከባቢ ተሰጥኦ ያላቸው ተተኪ አማተር ከያንያን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ቤት ጋር በቅንጅት በመሆን ላለፉት ተከታታይ 30 ቀናት መሰጠቱንም ገልፀዋል።

የኪነ ጥበብ ዘርፉ በማልማትና በማሳደግ የዞኑ ብሔረሰብ እሴቶችን ይበልጥ ለማስተዋወቅ በትኩረት እንደሚሰራ አክለው ገልፀዋል።

በቀጣይ በዘርፉ በርካታ ባለተሰጥኦ ወጣቶችን በማሰልጠንና ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት መስራት እንደሚገባ የገለፁት አቶ መሀመድ ጀማል የዞኑ ህዝብ ባህል፣ ታሪክ፣ እሴቶችን በተለያዩ መድረኮች ከማቅረብ በተጨማሪ ለወጣቶች የስራ እድል ለመፍጠርም እንደሚሰራ ተናግረዋል።

እንደ አቶ መሀመድ ገለፃ ተመራቂ ከያንያን በቀጣይ የራሳቸውን ሙያ ከማሳደግ ጎን ለጎን ተተኪ ለማፍራት መስራት እንዳለባቸው ጠቁመው የዞኑ ብሔረሰብ ባህል፣ታሪክና ትውፊቶችን በኪነ ጥበብ ዘርፋ ይበልጥ ማስተዋወቅ ይኖርባችኃል ሲሉ አሳስበዋል።

የጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ተመስገን ገብረመድህን በበኩላቸው ዞኑ የበርካታ ተፈጥሮአዊ፣ ሰው ሰራሽና ታሪካዊ ቅርሶችና እሴቶች መገኛ መሆኗን ገልፀው የብሔረሰቡ እምቅ ሀብቶችን በማልማት ማህበራዊ ጥቅም ላይ ለማዋል በኪነ ጥበብ ዘርፉ የተጀመሩ ስራዎች ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።

ኪነ ጥበብ የማህበረሰቡ ሀብት መሆኑን የገለፁት አቶ ተመስገን ዞኑ ለዘርፉ ምቹ በመሆኗ ብሔረሰቦቹ ኪነ ጥበብ ለደስታ፣ ለሰርግ፣ ለደቦ ስራ፣ ለእርቅ፣ ለዳኝነት እና ለሀይማኖታዊና ባህላዊ በዓላት እንደሚጠቀሙበት አስረድተዋል።

አክለውም ስልጠናው እንዲሳካ ድጋፍ ላደረጉ ለጉራጌ ዞን አስተዳደር፣ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር፣ ለወልቂጤ ዩኒቨርሲቲና ለሌሎችም ባለድርሻ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

ተመራቂዎችም ለዚህ ዕለት በመብቃታችሁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለው በሰለጠኑበት ሙያ ማህበረሰቡ በቅንነት እንዲያገለግሉ አሳስበዋል።

በምርቃት ስነስርአቱ የተገኙት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቲያትር ዋና ዳይሬክተር አቶ ማንያዘዋል እንዳሻው እንዳሉት በብሄራዊ ቴአትር ከ3 አመታት በላይ በመታየት ከፍተኛ አድናቆት ያገኘው የቃቄ ውርደወት ስራ በሀገር አቀፍ ብቻ ሳይሆን በአለም አቀፍ ደረጃ ሊታይ የሚገባው የትልቅ ታሪክ ባለቤቶች በመሆናችሁ ልትኮሩ ይገባል ብለዋል።

በዛሬው እለት የተመረቁ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች ያገኙትን እውቀት ተጥቅመው የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርሱ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ሊያደርጉላቸው እንደሚገባም አመላክተዋል።

አርቲስት መውደድ ክብሩ በምረቃ ስነስርአቱ ላይ ተገኝቶ በሰጠው አስተያየት ተመራቂዎቹ በመድረክ ያቀረቡትን የኪነ ጥበብ ስራ እንዳስደሰታቸውና ትልቅ አቅም እንዳላቸው ጠቁመው በቀጣይም ለዘርፉ ልዩ ትኩረት በመስጠት የብሔረሰቦቹ እምቅ ሀብት በመድረክ ለአለም ለማስተዋወቅ መስራት እንዳለባቸውና ለዚህም የሚመለከታቸው አካላትም ከቁሳቁስ ጀምሮ ድጋፍ ሊያደርጉላቸው ይገባል ብለዋል።

ከተመራቂዎቹ መካከል አቶ ሪያድ መሀመድ፣ራሄል አበራና አቶ ስንታየሁ ከበደ በጋራ በሰጡት አስተያየት ስልጠናው በአግባቡ ተከታትለው በመመረቃቸው መደሰታቸውን ጠቁመው በቀጣይም በኪነ ጥበብ ዘርፉ ያገኙትን እውቀት ተጠቅመው የዞኑ ብሔረሰብ እሴቶችንና ትውፊቶችን ይበልጥ ለማስተዋወቅ እንደሚሰሩም ገልፀዋል።

በየአከባቢያቸው መሰል ተተኪ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎችን ለማፍራት በቁርጠኝነት እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

በመጨረሻም በኪነ ጥበብ ዘርፉ ለተመረቁ ባለሙያዎችንና ስልጠናው እንዲሳካ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላት የእውቅና እና የምስክር ወረቀትና የተለያዩ ስጦታዎችን ተበርክቶላቸዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

በመረጃ ምንጭነት ገጻችን ምርጫዎ ስላደረጉ እናመሰግናለን!!

= ኢትዮጵያን እናልማ!
= የፈረሰውን እንገንባ!
= ለፈተና እንዘጋጅ!

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:-
https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *