የከተማው ህብረተሰብ የሚያነሳቸውን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ምላሽ ለመስጠት የንግዱ ማህበረሰብ ለታክስ ህግ ተገዢ በመሆን የሚጠበቅበትን ግብር በተገቢው መክፈል እንዳለባቸው የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ አሳሰቡ።

በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ አስተዳደር በታክስ ተገዢነት ላይ ከደረጃ ሀ እና ለግብር ከፋዮች ጋር ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የንቅናቄ መድረክ በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ እንዳሉት ሁሉም ዜጋ ለሀገሩ ብሎም ለአካባቢው ከሚያበረክተው አስተዋጽኦ አንዱ ግብርን በተገቢው መንገድ መክፈል ነው።

ገቢን በማሳደግ የከተማው ህብረተሰብ የልማት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት፣ የገቢ መሰረትና ኢንቨስትመንት ለማስፋት ብሎም ንግዱን ለማሳለጥ ህብረተሰቡ ለሰላም ዘብ መቆም ይገባል ያሉት አቶ ላጫ ከዚህም ባለፈ የከተማው ጽዳትና ውበት በመጠበቅ ሁሉም የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል ብለዋል።

እንደ አቶ ላጫ ጋሩማ ገለጻ ባለፈው 2 አመታት በተደረገው ጥናት 95 በመቶ የሚሆነው የንግዱ ማህበረሰብ ደረሰኝ እየሰጠ አለመሆኑ ተረጓግጧል ብለዋል።

የንግዱ ማህበረሰብ ቫት በተገቢው ሰብስበው ለመንግስት ገቢ እያደረጉ ባለመሆኑ ምክንያት የገቢ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆኑን ጠቅሰው ከዚህም ባለፈ የተሳሳቱ መረጃዎችን ማቅረብ፣ ህገወጥ ንግድ መበራከት እንደ ምክንያት አንስተዋል።

የንግዱ ማህበረሰብ ግብርን በተገቢው በመክፈልና ለታክስ ህግ ተገዢ በመሆን ግዴታቸውን መወጣት አለባቸው ያሉት አቶ ላጫ ይህም በተገቢው በማይወጡ ነጋዴዎች ላይ መንግስት ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድም አስገንዝበዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ ትምህርትና ስልጠና ዘርፍ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ተስፋዬ አሰፋ በመድረኩ ተገኝተው እንዳሉት ከታክስ ህግ ተገዢነት ችግሮች ውስጥ የግብይት ሂደቱ በደረሰኝ አለመሆን፣ ደረሰኝ የመስጠትና ጠይቆ የመቀበል ችግሮች በመኖሩ መንግስት ከዘርፉ ማግኘት የሚገባውን ገቢ በከፍተኛ ሁኔታ እያጣ ይገኛል ብለዋል።

ይህ ችግርም ክልሉና ዞኑ የሚያመነጫቸውን ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብ ወደ ልማት ለመቀየር ተግዳሮት መሆኑን ጠቁመው ለዚህም የክልሉ መንግስት በታክስ ህግ ተገዢነት ላይ ከንግዱ ማህበረሰብ ንቅናቄ በየደረጃው በማድረግ በዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለህዝብ ልማት እንዲውል ታሳቢ ተደርጎ እየተሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል።

በክልሉ ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ደረሰኝ ከመስጠትና ከመቀበል አኳያ ችግሮች መኖሩን ጠቅሰው የታክስ ህግ ተገዢነት ለማስፈጸም ከግብር ከፋዮች ጋር በአግባቡ በመግባባት ሀላፊነታቸው እንዲወጡና ግዴታቸውን በማይወጡ አካላት ላይ እርምጃ በመውሰድ የታክስ ስርአቱ በይበልጥ ውጤታማና ቀልጣፋ እንዲሆን እንደሚሰራ አመላክተዋል።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ እንዳለ ስጦታው እንዳሉት በታክስ ህግ ተገዢነት ሂደት ላይ ያጋጠሙ ችግሮች በመፍታት የክልሉና የዞኑ ኢኮኖሚ የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ ለመሰብሰብ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባል።

የከተማው ግብር ከፋይ ማህበረሰብ የታክስ ስወራና ማጭበርበርን በመከላከል የገቢ አሰባሰቡ ስኬታማ እንዲሆንና በከተማው የተጀማመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ለማፋጠን የንግዱ ማህበረሰብና ነዋሪው ብሎም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ገልጸዋል።

የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት የንግዱ ማህበረሰብ ገቢውን በማሳውቅ ከመክፈል ባለፈ የከተማው አገልግሎት ተጠቃሚዎች ደረሰኝ በመጠየቅ የድርሻቸውን እንዲወጡም አመላክተዋል።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አብድልከሪም መሀመድ በበኩላቸው የንቅናቄ መድረኩ አላማ በከተማው ከሚገኙ ደረጃ ሀ እና ለ ግብር ከፋዮች አጠቃላይ የግብር ስርአቱ ለማሳለጥ ብሎም ከደረሰኝ አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ለመቅረፍ ከከተማው የንግዱ ማህበረሰብ ጋር ውይይት በማድረግ መግባባት ለመፍጠር ያለመ ነው ብለዋል።

የከተማው እድገት ለማሳለጥና ከአቻ ከተሞች እኩል እንድትሆን ግብር ከፋዩ ግብይት በደረሰኝ የመገበያየት ባህሉ ማሳደግ ይኖርባቸዋል ብለው ለታክስ ተገዢ በማይሆኑ ግብር ከፋዮች ላይ አዋጅና መመሪያ መሰረት በማድረግ ህጋዊ እርምጃ እንደሚውሰድም ገልጸዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች እንዳሉት ግብር ከፋዩ የሚጠበቅባቸውን ግብር እንደሚከፍሉ ገልጸው የተሰበሰበውም ግብር ለታለመለት አላማ በማዋል ከተማዋ ከሌሎች ከተሞች እኩል እንድትሆን ያለባትን የመሰረተ ልማት ችግር መቅረፍ ይገባል ብለዋል።

በተለይም በከተማው ህገወጥ ነጋዴዎች መበራከትና በህጋዊ ነጋዴዎች ላይ አለታዊ ተጽዕኖ መፍጠሩ፣ ፍትሃዊ የሆነ የግብር ስርአት አለመኖር አንስተው ከዚህም ባለፈ የከተማው የውሃ፣ የመብራትና የመንገድ መሰረተ ልማት ችግሮችን ለመቅረፍ መሰራት አለበት ብለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *