የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት በጉራጌ ዞን እነሞርና ኤነር ወረዳ ከ76 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እያስገነባው የሚገኘው የጉስባጃይ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ እና መሰናዶ ትምህርት ቤት ግንባታ ከተያዘለት ጊዜ አስቀድሞ ለማጠናቀቅ እየተሰራ መሆኑ የክልሉ ርዕሰ መንግስት ገለፀ ፡፡

የትምህርት ቤቱ የግንባታ ሂደት የደረሰበት ደረጃ በኦሮሚያ ክልል፣ በጉራጌ ዞንና በእነሞርና ኤነር ወረዳ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተጎብኝቷል።

በጉበኝቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሻፊ ሁሴን እንዳሉት የትምህርት ቤቱ መገንባት የሁለቱ ብሔረሰቦች የቆየ የወንድማማችነትና የአብሮነት እሴቶች ለማጠናከር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።

ሀገሪቱ ማደግ የምትችለው በአንድ ክልል ወይም በአንድ አካባቢ ብቻ በተማረ የሰው ሀይል አለመሆኑን የገለጹት ኃላፊው ሀገሪቱ የምትፈልገው የተማረ የሰው ኃይል በእውቀትና በስነምግባር የታነጸ እንዲሆን ትምህርት ቤቶችን በስፋት መገንባት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን ምክትል ስራ አስኪያጅ አቶ ሸዋረጋ ጣፋ በበኩላቸው የቢሮው ባለሙያዎች ደረጃውን የጠበቀ የትምህርት ቤቱ ዲዛይን በነጻ የሰሩ ሲሆን አጠቃላይ የግንባታ ስራው በጥራትና በፍጥነት እንዲጠናቀቅ አስፈላጊውን ቁጥጥር እየተደረገለት ይገኛል ብለዋል።

አቶ ጥላሁን ኡርጌሳ የኦሮሚያ ኮንስተራክሽን ኮርፖሬሽን የግንባታ ቡድን መሪ ሲሆኑ የኦሮሚያ መንግስት በጉራጌ ዞን በእነሞርና ኤነር ወረዳ እያስገነባው ያለው የጉስባጃ ቀበሌ የአጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ እና መሰናዶ ትምህርት ቤት በ 12 ሄክታር ላይ እንዳረፈና የግንባታ ወጭውም 76 ሚሊየን ብር እንደሆነም አብራርተዋል።

አክለውም አቶ ጥላሁን ግንባታው ለማጠናቀቅ የተያዘለት የጊዜ ገደብ 7 ወር ቢሆንም አራት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ነው።

ለዚህም የግንባታ እቃዎች ሳይቋረጥ በፍጥነት በመላክና በመደገፍ ቶሎ ተጠናቆ ለህብረተሰቡ አገልግሎት እንዲሰጥ በቅንጅት ይሰራል ብለዋል ፡፡

ግንባታን መጀመር ብቻ ሳይሆን በተያዘለት የጊዜ ገደብ በማጠናቀቅ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ ይገባል ያሉት ቡድን መሪው የትምህርት ቤቱ የግንባታ ስራው ከተያዘላት የጊዜ ገደብ አስቀድሞ እንዲጠናቀቅ ይሰራል ብለዋል።

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ የኦሮሚያ ክልል መንግስት ወንድማማችነት እንዴት መተሳሰር እንዳለበት፣ ሀገራዊ አንድነት እንዴት መጠናከር እንዳለበት፣እንዴት አብሮ ማደግ እንደሚቻል ለማሳየት የጀመረው ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

የወንድም ህዝቦች የሰጡንን ፕሮጀክት እየደገፍን ከጎናቸው እየሆንን የትምህርት ቤቱ ግንባተ በታቀደለት የጊዜ ገደብ እንዲያልቅ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

የአከባቢው ማህበረሰብ የትምህርት ቤት ፕሮጀክቱን ለሚሰሩ ሰዎች አስፈላጊውን ትብብርና ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የእነሞርና ኤነር ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ያዕቆብ ግርማ በበኩላቸው የአከባቢው ማህበረሰብ በነበረበት የትምህረት ቤት ችግር ልጆቹን ወደተለያዩ አከባቢዎች ሄደው እንዲማሩ ይገደዱ ነበር ብለዋል።

የኢኮኖሚ አቅም ያላቸው ተማሪዎች ብቻ ቤት ተከራየተው ሲማሩ ሌሎቹ ደግሞ ከትምህርት ገበታ እርቀው በተለያየ የስራ መስክ ይሰማሩ እንደነበርም አብራርተዋል፡፡

ግንባታው ሲጠናቀቅ ለትምህርት ፍለጋ ረጅም እርቀት ሳይጓዙና ለወጪ ሳይዳረጉ ከቤተሰብ ጋር ሆነው የመማር እድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል፡፡

ያነጋገርናቸው የጉብኝቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የትምህርት ቤቱ ግንባታ የሁለቱን ብሔረሰቦች ትስስር ከማጠናከሩ በተጨማሪ ለትምህረት ፍለጋ የሚወጣ ወጪን እንደሚቀንስና እንዲሁም በኢኮኖሚ እጥረት ምክንያት ትምህርት የሚያቋርጡ ተማሪዎችን ይታደጋል ብለዋል።

በጉብኝቱ የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች፣የጉራጌ ዞን የዞኑ ም/አስተዳዳሪና የዞኑ ግብርና መምሪያ ሀላፊ አቶ አበራ ወንድሙ፣የእነምርና ኤነር ወረዳ ዋና አስተዳመሪ አቶ ያቆብ ግርማና ሌሎችም የተለያዩ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የአከባቢው ነዋሪዎች ተሳትፈዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *