የባህልና ስፖርት ሚኒስተር ከወልቂጤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ከጉራጌና ከየም ዞን፣ከቀቤና ልዩ ወረዳ፣ከማእከላዊ ኢትዩጵያ ክልል በጋራ በመሆን በቆዳ እደ ጥበብ ስራ ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቀቀ።
የባህልና ስፖርት ሚኒስተር የኪነ ጥበብ ስነ ጥበብና የፈጠራ ልማት ዘርፍ ሚኒስቴር ዴኤታ ወ/ሮ ነፊሳ አልማዲን እንደገለጹት የእደ ጥበብ ስራዎች ባህልን ከማስተዋወቅ በተጨማሪ የኢኮኖሚ ማስገኛ እየሆኑ በመሆኑ ዘርፉን ማነቃቃት ይገባል ብለዋል።
በዘርፉ ለተሰማሩ የእደ ጥበብ ማህበራት ምቹ ቦታ ማዘጋጀትና የገበያ ትስስር በማመቻቸት ለወጣቶችና ሴቶች የስራ እድል መፍጠር እንደሚገባ የመከሩት ወ/ሮ ነፊሳ የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲደረግላቸው ከፖሊ ቴክኒክ ኮሌጆችና ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
የጉራጌ ዞን ዋና የመንግስት ተጠሪ አቶ ክብሩ ፈቀደ እንደገለፁት ባህል ለልማት፣ለሰላምና ለአንድነት ትልቅ ሚና ይጫወታል።በሀገራችንም በርካታ የእደ ጥበብ ስራዎች ያሉ ሲሆን እነዚህም ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር በማዛመድ የሀገር ሀብት ማድረግ እንደሚገባ አስታውቀዋል።
እነዚህ የጥበብ ስራዎች “የይቻላል” መንፈስ የታየባቸው የትጋት ውጤቶች ናቸው ያሉት አቶ ክብሩ ሰልጣኞችም የሰለጠኑት ስልጠና ወደ ማህበረሰቡ አውርደው እንዲሰሩና የዞኑ መንግስትም ለእነዚህ ባለሙያተኞች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
የማእከላዊ ኢትዩጵያ ክልል ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ አቶ ሳሙኤል መንገሻ የባህል ኢንድስትሪው የምርት ውጤቶች በጥራትም ሆነ በብዛት በማሳደግ ለሀገር እና ለአለም አቀፍ ገበያ በማቅረብ የባህሉ ዘርፍ የራሱ ድርሻ እንዲወጣ ያደርጋል።
ቀጣይ በክልሉ በጨርቃ ጨርቅ፣በሸክላና በቀርከሀ ውጤቶች ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ጋር በመነጋገር በዘርፉ ላሉ አካላት ውጤታማ እንዲሆኑ እንስራለን ነው ያሉት።
ጉራጌ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ መሰረት አመርጋ እንደገለፁት ሀገራችን ሰፊ የቆዳ ምርት ያላት ብትሆንም ወደ እደ ጥበብ ስራዎች ቀይሮ የህብረተሰቡ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንጻር ውስንነት እንዳለ ጠቅሰዋል።
መምሪያው የእደ ጥበብ ዘርፉን ለማዘመን ከወልቂጤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ጋር ተቀናጅቶ እየሰራ መሆኑን ያመላከቱት ወ/ሮ መሰረት ህብረተሰቡ በዘርፉ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ እንዲሆን በትኩረት እንሰራለን ነው ያሉት።
የወልቂጤ ፖሊቴክኒክ ኮሌጅ ዲን አቶ ኸይሩ አህመዲን የእደ ጥበብ ዘርፍ የሚሰሩ ስራዎች የበለጠ ውጤታማ እንዲሆኑ የክህሎት የአመለካከትና የቴክኖሎጂ ሽግግር በመፍጠር ዘርፉን እንዲነቃቃ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
ምርቃቱ ሲከታተሉ ያገኘናቸው ሰልጣኞች እንዳሉት ስልጠናው የእደ ጥበብ ክህሎታቸው የበለጠ እንዳሳደገላቸው እና በቀጣይ የኢኮኖሚ ማሰገኛ አድርገው እንደሚጠቀሙበት ተናግረዋል።
መንግስትም የገበያ ትስስር በመፍጠር፣የመሸጫ ቦታዎችን ማመቻቸትና ዘርፉ እንዲደግፍ አሳስበዋል።