የእንስሳት ዝርያ በማሻሻል የአርሶአደሩ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከመቼዉም ጊዜ በላይ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

መስከረም 05/2015 ዓ.ም

የእንስሳት ዝርያ በማሻሻል የአርሶአደሩ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ ከመቼዉም ጊዜ በላይ በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

የተሻሻለ የእንስሳት ዝርያ ያላቸው ከብቶች በማርባት ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ በጉራጌ ዞን የሚገኙ አርሶ አደሮች ተናገሩ።

የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ መሀመድ ሙደሲር እንደገለፁት በጉራጌ ዞን ከሚገኙ 2 ነጥብ 8 ሚሊዮን የቀንድ ከብቶች ዝርያቸው የተሻሻለው 11በመቶ የሚሆኑት ብቻ ነው።

ይህንን ዝቅተኛ የሆነው የተሻሻለ የእንስሳት ዝርያ ቁጥር በማሳደግ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ነው። በ2014 ዓ.ም በመደበኛ ሰው ሰራሽ ፣ በተሻሻለ ኮርማና በሆርሞን ማድራት ቴክኖሎጂ 9ሺህ 839 ክልስ ጥጆች ማግኘት እንደተቻለም ገልጸዋል።

አርሶ አደሩ ብዛት ያላቸው የሀበሻ ከብቶች በማርባት የሚያገኙት ምርት ዝቅተኛ መሆኑን ተገንዝበው የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው እንስሳት በማርባት የእንቁላል፣ የስጋና የወተት ምርታማነታቸውን እያሳደጉ ሲሆን የወተት ምርታማነቱ በቀን ያገኙት ከነበረው ከ 1 ነጥብ 5 ሊትር ወደ 14 ነጥብ 5 ሊትር ማሳደግ እንደቻሉ ምክትል ኃላፊው አስረድተዋል።

በመሆኑም በተጠናቀቀው በጀት አመት በገበያ ላይ የሚስተዋለው የእንስሳት ተዋጽኦ እጥረት ለመቅረፍ በተሰራው ስራ 33ሺህ 64 ቶን ስጋ፣ ከ4ሺህ 310 ቶን በላይ እንቁላል እና 99 ሺህ 107 ቶን ወተት በማምረት ለህብረተሰቡ ማቅረብ ተችሏል ብለዋል።

የእንስሳት ምርታማነት ለማረጋገጥ የፈሳሽ ናይትሮጂንና የአባለ ዘር እጥረት እንዲሁም የአዳቃይ ቴክኒሽያን ብቃትና ተደራሽነት ችግር ሊቀረፍ እንደሚገባ አመላክተዋል።

የእንስሳት ምርታማነት ለማረጋገጥ በአሁን ወቅት የሚስተዋለው የመኖ አቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ 10 ሺህ 16 ሄክታር መሬት በተሻሻለ መኖ ማልማት ተችሏል ብለዋል።

የእዣ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዘውዱ ዱላ እንዳሉት የእንስሳት ዘርፍ ውጤታማ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በወረዳው የተሻሻለ የእንስሳት ዝርያ ያላቸው ከብቶች የሚያረቡ አርሶአደሮች ቁጥር እያደገ በመምጣቱ የእንስሳት አዳቃይ ባለሙያዎች በመመደብ አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ ብለዋል።

በወረዳው የሚስተዋለው የግብዓት አቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ አርሶ አደሩ ባለው አነስተኛ ማሳ መኖ እንዲያለማ እየተሰራ ሲሆን እስካሁን ከ2 መቶ እስከ 1 ሺህ ካሬ ሜትር ላይ በተሳተፉ አርሶ አደሮች 789 ሄክታር መሬት በተሻሻለ የመኖ ዘር እንደለማ ገልጸዋል።

በመሆኑም ከዚህ ቀደም ይስተዋል የነበረው የወተት ምርት አቅርቦት እጥረት መቀነስ መቻሉን አቶ ዘውዱ ተናግረዋል።
አቶ ደንድር ፍታ እና አቶ አብዛ ንማኒ በጉራጌ ዞን የእዣ ወረዳ ነዋሪ ሲሆኑ ዝርያቸው የተሻሻለ እንስሳት ማርባት ከጀመሩ ወዲህ ተጠቃሚ መሆናቸዉን ገልፀዋል።

ነባር ወይም የሀበሻ ከብቶች የወተት ምርታማነታቸው ዝቅተኛ በመሆኑ ከቁጥር የዘለለ ጠቀሜታ እንደማያስገኙ አርሶ አደሮቹ ተናግረዋል።

እንደ አርሶ አደሮቹ ገለጻ በግብርና ባለሙያዎች ግንዛቤ ተፈጥሮላቸው የሀበሻ ከብቶች የተሻሻለ ዝርያ ባላቸው ከብቶች በመተካት የተሻለ የወተት ምርት እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።

በመሆኑም የወተት ምርት ተዋጽኦ አቅርቦት እና ፍላጎትና ባለመጣጣሙ አርሶአደሮች ከራሳቸው ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸውን ለማሳደግ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው ከብቶች ማርባት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

ሌሎች አርሶ አደሮች ከእንስሳት እርባታው ጎን ለጎን የወተት ምርታማነትና የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው ጥጆች ለማግኘት ባላቸው አነስተኛ ማሳ መኖ እንዲያለሙ ተሞክሯቸውን አጋርተዋል ሲል የዘገበዉ የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ነዉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *