የመምሪያው የ2014 የግማሽ አመት ዕቅድ አፈፃፀም በወልቂጤ ከተማ ተገመገመ።
የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ሀላፊ አቶ ሸምሱ አማን በግምገማ መድረኩ ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር በወሊድ ወቅት በሚከሰተው የደም መፍሰስ ምክንያት ለህልፈት የሚዳረጉ እናቶች ቁጥር በመቀነስ ጤናቸው እንዲጎለብት እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
ለዚህ ደግሞ የጤና ባለሙያዎችና የተቋማቱ አመራሮች ሚና የጎላ መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው በህጻናት ላይ የሚከሰተው ሞት ለመቀነስ ትኩረት ከሰጡት ይገባል ብለዋል።
የጉባኤው አላማ አፈጻጸም መገምገም ብቻ ሳይሆን የዞኑ ማህበረሰብ በጤናው ዘርፍ ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲያገኝ የተሰሩ ስራዎች ተሞክሮ ማስፋትና በአፈጻጸም ሂደትም ጉድለቶችን በመሙላት በሚቀጥለው ግማሽ አመት የተሻለ ስራ መስራት ይገባል ብለዋል።
መምሪያው በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ጤና ለማጎልበት የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ለማጠናከር እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
መንግስት ዜጎች በህመማቸው ልክ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ከነደፋቸው ስትራቴጂዎች አንዱ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አገልግሎት ነው።
በጤና መድህን አሠራር ዜጎች ጤናማ በሚሆኑበት ወቅት በሚከፍሉት አነስተኛ መዋጮ የጤና እክል በሚያጋጥማቸው ወቅት ከመድህን ቋቱ ወጪ በሚደረግ ገንዘብ የጤና ወጪአቸው የሚሸፈን በመሆኑ የተሰበሰበው ገንዘብ ወደ ባንክ ገቢ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡
አቶ አመነ ወልዴ በመምሪያው የበሽታ መከላከል ዋና የስራ ሂደት አስተባሰሪ ሲሆኑ ባለፉት ስድስት ወራት የተከናወኑ ተግባራት የተሻለ አፈጻጸም ማስመዝገብ ተችሏል ብለዋል።
ዞኑን በጤና ተግባራት ሞዴል ለማድረግ ግብ ተጥሎ እየተሰራ ነው ያሉት አቶ አመነ በወረዳ ትራንስፎርሜሽን፣ በመረጃ አብዮት እና በሌሎች ተግባራት በመፈጸም እንዲሁም ወረዳዎች የልምድ ልውውጥ በማድረግ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ የግምገማ መድረኩ መልካም አጋጣሚ ይፈጥራል ብለዋል።
መምሪያው የእናቶች ጤና ለማጎልበት ከሚሰራቸው ስራዎች አንዱ የማህጸን ወደ ውጭ የመውጣት ችግር ተጋላጭ እናቶች የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ከወልቂጤ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል እነሱ ከቡታጅራ አጠቃላይ ሆስፒታል ጋር ውል ተገብቶ እየተሰራ ነው።
በጉባኤው ከተነሱ ጉዳዮች መካከል የሪፖርት ጥራት፣ የአገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ማሻሻልና የወረዳ ትራንስፎርሜሽን በመሆናቸው በተያዘው ግማሽ አመት ትኩረት እንደሚሰጣቸው አብራርተዋል።
የጉመር ወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አሸናፊ ቢረጋ እና የጉንችሬ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ተሻለ ንጋቱ በሰጡት አስተያየት ጉባኤው ጠንካራና ደካማ አፈጻጸም የተለየበት፣ ልምድ ያካፈሉበትና ተሞክሮ የቀሰሙበት መድረክ እንደሆነ ገልጸዋል።
በወረዳው የሚነሱ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት ለማሻሻል በትኩረት በመሰራቱ አበረታች ውጤት ማስመዝገብ እንደተቻለ ገልጸዋል።
በወረዳው 13 ቀበሌዎች ሞዴል ማድረግ መቻሉን የተናገሩት አቶ አሸናፊ በቀጣይ ወረዳው ሞዴል ለማድረግ እንደሚሰሩ ገልጸዋል።
ከሆስፒታል ጋር ያለው ትስስር እና ከመድሀኒት እጥረት ጋር ተያይዞ ህብረተሰቡ የሚያነሳቸው ጥያቄዎች ለመመለስ ይሰራል ብለዋል።