የአገና ከተማ እድገትን ለማፋጠን የህብረተሰቡንና የመንግስት አቅምን አቀናጅቶ በተሰሩ ስራዎች ውጤት ማስመዝገባቸው የአገና ከተማ አስተዳደር አስታወቀ።


በህብረተሰብ ንቁ ተሳትፎና በመንግስት በተገኘ ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ለብዙ አመታት የመልካም አስተዳደር ችግር ሆነው የቆዪ የመሰረተ ልማት ስራዎች መስራታቸውን የአገና ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት ጠቁሟል።

የጉራጌ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ መኔጅመብት አካላት የአገና ከተማ የመሰረተ ልማት ስራዎችን ተዟዙረው ተመልክተዋል።

የአገና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሀብቴ ዘርጋ እንደገለጹት የአገና ከተማ አስተዳደር ከሆነ ወዲህ 40 በመቶ በህብረተሰብ ተሳትሮ 60 በመቶ በመንግስት በሚል የከተማ የመሰረተ ልማት ስትራቴጂን እውን ለማድረግ ህብረተሰቡን በማወያየት እና ወደ ተግባር በመግባት ውጤታማ ስራዎችን መስራት ተችሏል ብለዋል ።

የአገና ከተማ እድገትን ለማፋጠን የህብረተሰቡንና የመንግስት አቅምን አቀናጅቶ በተሰሩ ስራዎች ውጤት ማስመዝገባቸው የገለጹት የአገና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሀብቴ ዘርጋ በዚች 2 አመታት ውስጥ ህብረተሰቡን በማሳተፍ የኮብል ድንጋይ ንጣፍ፣ የውስጥ ለውስጥ የጥርጊያና የከፈታ ስራዎች፣ የመብራትና ውሃ መስመር ዝርጋታ፣ የውሃ ማፋሰሻ ዲችና የቢሮ የቄራን ለተለያዩ አገልግሎት የሚውሉ የግንባታ ስራዎችን መሰራታቸውን አብራርተዋል።

አክለውም በከተማው ኢንቨስትመንት ለመሳብ የመሬት ዝግጅት ስራ መሰራቱና ባለሀብቶች እንዲያለሙ ምቹ ሁኔታ እየተፈጠረ ይገኛል ያሉ ከንቲባው የአገና ከተማ ውስጥ እየተሰሩ ባል የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች የህብረተሰቡ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ እየጨመረ መምጣቱን ገለፀዋል።

የጉራጌ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ምክትል ኃላፊና የማስፈጸም አቅም ግንባታና መሰረተ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ የሆኑት አቶ አድማሱ ፍቅሬ እንደገለጹት አገና ከተማ ከተማ አሰተዳደር ከሆነች ጊዜ ጀምሮ በመንግስትና በህብረተሰቡ ተሳትፎ አመርቂ የልማት እንቅስቃሴ እየታየባት መሆኑ ተናግረዋል።

በከተማው ለኢንቨስትመን የታቀዱ ፕሮጀክቶች ጸድቀው በአፋጣኝ ወደስራ እንዲገቡ መምሪያው ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በትኩረት እንዲሚሰራ የተናገሩት አቶ አድማሱ በመምሪያው እየተደረጉ ያሉ ድጋፍ ክትትሎች ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

አገና ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤት ኃላፊ አቶ ተክሉ አብሽር በበኩላቸው በተያዘው በጀት አመት ብቻ በህብረተሰብ ንቁ ተሳትፎና በመንግስት በተገኘ ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ በርካታ የልማት ስራውች ተሰርቷል ነው ያሉት።

ከነዚህም የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ 300 ሜትር የዲች ግንባታ፣ 2 ነጥብ 5 ኪሎ ሜትር አዲስ የመንገድ ከፈታና ጥርጊያ ስራ፣ 1 ነጥብ 9 ኪሎ ሜትር የመብራት ዝርጋታ፣ 4 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የውሃ መስመር ዝርጋታ፣ እንዲሁም 1 ነጥብ 9 ሄክታር መሬት የማዘጋጀትና የመሳሰሉ የመሰረተ ልማት ስራዎች መስራታቸውን አብራርተዋል።

የሚሰሩ የመሰረተ ልማት ስራዎች ጥራታቸው እዲጠበቅ ለማድረግ በከተማው የመሀንዲሶች ቡድንና ከህብረተሰቡ የተውጣጡ ኮሚቴዎች መዋቀራቸውና ከጉራጌ ዞን ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን መምሪያ ጋር ተቀናጅተው እየሰሩ መሆኑንም አክለው ተናግረዋል።

አቶ ብርሃኑ ብርሼ፣ አቶ ከበደ ሽኩር፣ አቶ ሲሳይ የአገና ከተማ ነዋሪዎች ናቸው።በጋራ በሰጡት አስተያየት 40 በ60 የተሰኘው የከተማ ልማት ዝርጋታ ስትራቴጂን በመጠቀም ከተማዋን ለመቀየር ከራሳቸው ጨምሮ መላው የከተማውና ከከተማው ውጪ ያሉ የወረዳው ተወላጆች ባላቸው የገንዘብ ፣ጉልበትና እውቀት እገዛ እያደረጉ መሆኑን ተናግረዋል ።

በተደረገው ርብርብ ለብዙ አመት ህዝቡ የልማት ጥያቄ የነበሩ የመሰረተ ልማት ስራዎች ማለትም የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ፣ የዲች ግንባታ፣ አዲስ የመንገድ ከፈታና ጥርጊያ ስራ፣ የመብራት ዝርጋታ፣ የውሃ መስመር ዝርጋታ፣የኢንቨስትመንት መሬት የማዘጋጀትና የመሳሰሉ ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀዋል።

ከተማዋ ሌሎች ያደጉ ከተሞች የደረሱበት ደረጃ እንድትደርስ እያደረጉት ያለው ንቁ ተሳትሮ አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አብራርተዋል ሲል ዘገበው የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *