የአካባቢ ማህበረሰብና ባለሀብቱ በመሰረተ ልማት ዝርጋታ ላይ እያደረገ ያለው ተሳትፎ በማጠናከር የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት ለማሳደግ እንደሚሰራ የቸሃ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ።

በ2015 በጀት አመት ከ33 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የመንገድ ግንባታ ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የወረዳው ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

በጉራጌ ዞን በህብረተሰብ እና ባለሀብቶች ተሳትፎ የመንገድ መሰረተ ልማት በስፋት ከሚከናወንባቸው አካባቢዎች አንዱ የቸሃ ወረዳ ሲሆን በየ አመቱ የተለያየ ደረጃ ያላቸው መንገዶች እየተገነቡ ነው።

የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጥላሁን ሽምነሳ ማህበረሰቡ በመንገድ ግንባታ ስራ የካበተ ልምድ ያለው ሲሆን በ2015 ዓ.ም በማህበረሰብ፣ በባለሀብቶችና በመንግሥት ተሳትፎ ከ51 ኪሎ ሜትር በላይ የጠጠር መንገድ በማስገባት ለአገልግሎት ክፍት ማድረግ ተችሏል።

የወረዳው አስተዳደር ህብረተሰቡ በመንገድ ስራ የሚያደርገው ተሳትፎ ከማጠናከር በተጨማሪ የገንዘብ ፣ የግብዓት አቅርቦት እና የድጋፍና ክትትል ስራዎች እየሰራ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

ህብረተቡ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች ተጠቃሚ ለማድረግ የመንገድ መሰረተ ልማት ከፍተኛ ፋይዳ ያለው በመሆኑ ማህበረሰቡ፣ ባለሀብቱና መንግስት ተሳትፏቸው ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑ ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

በመሆኑም በወረዳው በተለያዩ አካባቢዎች በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ መንገዶች ዘላቂ አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ ህብረተሰቡ የተጎዱ መንገዶች መጠገን፣ በጎርፍ እንዳሸረሸሩ ክብካቤ ማድረግ እና የጎርፍ ማፋሰሻዎች መስራት እንደሚጠበቅበት አቶ ጥላሁን አሳስበዋል።

የወረዳው ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደሱ ድንቁ በበኩላቸው ህብረተሰቡ በመንገድ ግንባታ ላይ ያለውን ተሳትፎ በየአመቱ እያደገ በመምጣት የመንገድ መሰረተ ልማት ለማስፋፋት እየተሰራ ይገኛል።

በወረዳው የማህበረሰቡ፣ የባለሀብቱ እና የመንግስት አቅም በመጠቀም የድልድይ፣ የጠጠር መንገድ ግንባታ፣ የመንገድ ከፈታና የተለያዩ አነስተኛ ስትራክቸሮች መስራት መቻሉን ኃላፊው አስረድተዋል።

በበጀት አመቱ 33 ሚሊዮን 287 ሺህ 167 ብር ከመንግሥት፣ ከአካባቢው ማህበረሰብና ከባለሀብቶች በማሰባሰብ ከ51 ኪሎ ሜትር በላይ የጠጠር መንገዶችና ድልድዮች በማስገንባት ቀበሌ ከቀበሌ እና ቀበሌ ከዋና መንገድ በማገናኘት የህብረተሰቡን የእለት ተዕለት እንቅስቃሴ እንዲፋጠን መደረጉ አቶ ደሱ ገልጸዋል።

የወረዳው ባለሀብቶች እና ማህበረሰብ በመንገድ ልማት ላደረጉት ተሳትፎ አመስግነው በቀጣይ በተለያዩ ቀበሌዎች የመንገድ መሰረተ ልማት ለማስፋፋት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

አቶ ትዛዙ ነጋ እና አዲሱ ንስቁ የሰስየ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆኑ የመንገድ መሰረተ ልማት ባለመስፋፋቱ ህብረተሰቡ ለማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች ተጋላጭ እንዲሆን አድርጎት እንደነበር ገልጸዋል።

እንደነዋሪዎቹ ገለፃ የህብረተሰቡን የመንገድ ችግር ለመቅረፍ የአካባቢው ተወላጆች፣ ባለሀብቶች እና ነዋሪዎች ያላሰለሰ ጥረት በማድረግ ደረጃውን የጠበቀ የጠጠር መንገድ ማስገባት ችለዋል።

የመንገዱ መገንባት አርሶአደሮች ያመረቱትን ምርት በቀላሉ ወደ ገበያ ለመውሰድ የሚያስችላቸው ሲሆን ነፍሰጡር እናቶችና ሌሎች ህክምና የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች ወደ ጤና ተቋም በመሄድ አስፈላጊውን አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል ብለዋል።

የሲስና እማትየ ቀበሌ ነዋሪ ወጣት ፈለቀ ወልዴ እና የአዶሼ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ወይዘሮ ዘህዳት አክመል ከዚህ ቀደም የነበረው የመንገድ ችግር በእለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው ተጽዕኖ እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።

መንግስት ከማህበረሰቡ ጋር በመተባበር ያስገነባው መንገድ በማህበራዊ እና በኢኮኖሚ ዘርፎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል።

ስለሆነም በመንገድ ልማት የጀመሩት ቅንጅታዊ አሰራር በሌሎች መሰረተ ልማቶች ተግባራዊ እንደሚያደርጉ ገልጸዋል ሲል የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ዘግቧል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *