የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት በማሻሻል ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

መስከረም 21/2015

የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት በማሻሻል ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።

በዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል የተመራው ልዑክ በቸሀ ወረዳ በክላስተር የለማው የጤፍ ማሳ የመስክ ምልከታ አካሄደ።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት አርሶ አደሮች የባለሙያዎች ምክረሀሳብ ተግባራዊ ማድረግ በመቻላቸው በዘንድሮ የመኸር ወቅት የተመዘገቡ ውጤቶች አበረታች መሆናቸውን ገልጸዋል።

አርሶ አደሮች ከዝናብ ጠባቂነት ተላቀው በአመት ሶስት ጊዜ በማምረት የምግብ ዋስትናቸውን ማረጋግጥ እንዲችሉ የመስኖ ልማት ስራዎች ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን ዋና አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

በግብርናው ዘርፍ የሚስተዋሉ የማዳበሪያና ምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረት፣ የመካናይዜሽንና አማራጭ የመስኖ ልማት ስራዎች አለመስፋፋት በአርሶ አደሮቹ ተጠቃሚነት ላይ ተፅዕኖ ቢኖራቸውም የአርሶ አደሮች ክህሎት እያደገ በመምጣቱ በምርትና ምርታማነት እድገት ላይ እየተመዘገበ ያለው ውጤት አበረታች መሆኑን አቶ መሀመድ አስረድተዋል።

የዞኑ ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ በዞኑ በመኸር ወቅት በተለያዩ ሰብሎችና ለመሸፈን ከታቀደው ከ148 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት ከ144ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በሰብል የተሸፈነ ሲሆን ቀሪው ማሳ በሽምብራና በጓያ ሰብልና ለመሸፈን እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የአርሶ አደሮች ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የጤፍ፣ የስንዴ፣ የገብስና የባቄላ ሰብሎች በኩታገጠም እንዲለሙ መደረጉን የገለጹት ኃላፊው በዞኑ በክላስተር ከለማው ማሳ 24 ሺህ 788 ሄክታር መሬት በጤፍ ተሸፍኗል ብለዋል ።

እንደ ኃላፊው ገለጻ ኩታገጠም የአመራረት ዘዴ አርሶ አደሮች ግብዓት በተመሳሳይ ወቅት እንዲያገኙ ከማስሻል ባለፈ ሰብልን ከአረምና ከተባይ በጋራ በመከላከል የተሻለ ምርት ለማግኘት ያስችላቸዋል።

በበልግና በመኸር ወቅቶች የነበረው የማዳበሪያና የምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረት ለመቅረፍ አርሶ አደሮች አማራጭ ዝርያዎች እና ግብዓት እንዲጠቀሙ ተደርጓል ብለዋል።

በዞኑ የምርጥ ዘር አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት በአበሽጌ ወረዳ ከ350 ሄክታር በላይ መሬት የፓይነር ዝርያ ያላቸው የበቆሎ ሰብልና እየለማ ሲሆን የጤፍና የስንዴ ምርጥ ዘር ለማምረት በትኩረት እየተሰረሰ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል።

በዞኑ በመኸር ወቅት በዘር ከተሸፈነው ማሳ 7 ነጥብ 1 ሚሊዮን ኩንታል ምርት እንደሚጠበቅ የገለፁት አቶ ወንድሙ አመራሮችና ባለሙያዎች አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

በጉብኝቱ የተሳተፉት የዞኑ ዋና አፈጉባኤ ክብርት አርሺያ አህመድ በቸሀ ወረዳ በክላስተር የለማው የጤፍ ማሳ ውጤታማና በአርአያነት የሚጠቀስ በመሆኑ ሌሎች አርሶ አደሮች ልምድ መውሰድ አለባቸው ብለዋል።

የዞኑ ምክርቤት ቋሚ ኮሚቴዎች የግብርናው ዘርፍ ለማሳደግና በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች በመለየት ለአስፈጻሚ አካላት መረጃ ከመስጠት በተጨማሪ አስፈላጊውን ክትትል ለማድረግ እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የቸሀ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙራድ ከድር እንደገለጹት አርሶ አደሮች ከምግብ ፍጆታ ባለፈ ለገበያ በማቅረብ የገቢ አቅሙን እንዲጎለብት አመራሩ በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል።

ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ አርሶአደሮች ሜካናይዜሽንና ሙሉ ፓኬጅ እንዲጠቀሙ ከማድረግ በተጨማሪ አረምና ተባይ መቆጣጠር እንዲችሉ ግንዛቤ ተፈጥሮላቸዋል ብለዋል።

ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴ ለምርትና ምርታማነት እድገት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ በኩታገጠም የለማው ማሳ በትራክተር ማሳረስ እንደቻለ አስረድተዋል።

የአርሶ አደሮቹ የግብዓት አጠቃቀም እየተሻሻለ በመምጣቱ በተያዘው የመኸር ወቅት የተሻለ ምርት እንደሚጠበቅ የገለፁት አቶ ሙራድ አርሶ አደሮች የአረምና ተባይ ቁጥጥርና ስራው ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

በመስክ ምልከታ ወቅት ያነጋገርናቸው አርሶአደሮች በቤተሰብ ጉልበትና በደቦ መስራት በመቻላቸው ሰብላቸው የተሻለ አቁመናል እንዲኖረው አስችሎታል ብለዋል።

በቀጣይ ሰብሉ እስኪሰበሰብ ድረስ ሳይታክቱ እንደሚሰሩ ገልጸዋል አርሶ አደሮቹ።

ኩታገጠም የአስተራረስ ዘዴ ማሳቸው ለመንከባከብ፣ ግብዓት ለማግኘትና ልምድ ለመለዋወጥ ስለሚያስችላቸው በቀጣይም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *