የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ የሚያስችሉ የግብርና ግብዓቶች በማቅረብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ እየሰራ መሆኑን አድማስ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን አስታወቀ፡፡

ዩኒየኑ በሀገሪቱ የተከሰተውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት የሚያስችሉ መሰረታዊ የፍጆታና የግንባታ እቃዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ በማቅረብ ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝ ተገለጸ፡፡

የአድማስ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን ስራ አስኪያጅ አቶ አበበ አመርጋ የዩኒየኑ የስራ እንቅስቃሴ አስመልክተው በሰጡት መግለጫ እንዳሉት በ3 የሰው ሀይል፣ በ1700 የተናጠል አባላት፣ በ7 አባል ማህበራት፣ በ153 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል በመያዝ በ1995 ዓመተ ምህረት ተመስርቶ ስራውን የጀመረ ሲሆን አሁን ላይ በ42 የሰው ሀይል፣ በ52 ሺህ 299 የተናጠል አባል፣ በ145 አባል ማህበራት በማፍራት ያለው የካፒታል መጠን 27 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ነው፡፡

ዩኒየኑ ከተመሰረተበት ጊዜ ጀምሮ የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂዎችንና ግብዓቶችን በማቅረብ የኢኮኖሚ አቅማቸውን ለማሳደግ እንዲሁም የሚያመርቱት ምርት በወቅቱ የገበያ ዋጋ በመሽጠት ተጠቃሚ እንዲኑ እየተሰራ ይገኛል፡፡

በሀገሪቱ የተከሰተውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት የሚያስችሉ መሰረታዊ የፍጆታ እቃዎች በተመጣጣኝ ዋጋ ለህብረተሰቡ በማቅረብ ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝ የገለጹት አቶ አበበ በአድማስ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን ከኑግ ብቻ የሚመረተውና እጅግ ለጤና ተስማሚ የሆነው የቸምና ዘይት በወቅቱ የገበያ ዋጋ በሊትር 230 ብር ከሚሸጥበት ወደ 180 ብር ዝቅ በማድረግ በዩኒየኑ ሱቆች እየተሸጠ ይገኛል፡፡

በቀጣይም የግንባታ እቃዎች በማቅረብ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ ለማድረግ በዝግጅት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።

በተያያዘ የጉራጌ ዞን የመንግስት ሰራተኞች በሁለት ወር ክፍያ የቸምና ዘይት እየወሰዱ እንዲጠቀሙ የብድር አገልግሎት መመቻቸቱን የጠቆሙት ስራ አስኪያጁ ይህ እድል ለአጭር ጊዜ ብቻ የሚቆይ በመሆኑ ሁሉም ሰራተኞች ተጠቃሚ እንዲሆኑ አሳስበዋል፡፡

እንደ አቶ አበበ አመርጋ መግለጫ የቡና መፈልፈያ ፋብሪካ ተክሎ በዞኑ የሚመረተው ቡና በመፈልፈል ለማዕከላዊ ገበያ ለማቅረብ በትኩረት እየሰራ የሚገኝ ሲሆን አካባቢ የሚበክሉ የወዳደቁ የሀይላንድ ቆሻሻ ፕላስቲኮችን በመሰብሰብ እየፈጨ ለፋብሪካ ጥሬ ግብዓትነት ለሚጠቀሙ አካላት በመሸጥ ገቢ ከማግኘቱም ባለፈ አካባቢው እንዳይበከል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡

በቀጣይ የላወንደሪ ወረቀትና የተለያዩ ፌስታሎች በተለይም በዞኑ የሚገኙ የውሃ ፋብሪካዎች ለማሸጊያነት የሚጠቀሙት ላውንደሪ ወረቀት ለማምረት በዝግጅት ላይ እንደሚገኝ ገልጸው ዩኒየኑ የዞኑ አርሶ አደሮች በመሆኑ የሚጠበቅበትን አገልግሎት ለአባሉና ለህብረተሰቡ ማቅረብ እንዲችል የሚመለከተው ባለድርሻ አካላት አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርጉለት እንደሚገባ አቶ አበበ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአድማስ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን የቸምና ዘይት ፋብሪካ የላብራቶሪ ተክኒሻን ባለሙያ አቶ ፋሲል ታረቀኝ ስለ ቸምና ዘይት የጥራት ደረጃ አስተያየት እንዲሰጡን ጠይቀናቸው እንደተናገሩት የኑግ ሰብል በመሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበራት አማካይነት በአርሶ አደር ደረጃ ጥሩ ዝርያ በተስማሚ የአየር ንብረት እየተመረተ ስለ መሆኑ ክክትትል በማድረግ የጥራት ደረጃው በላብራቶሪ ከተረጋገጠ በኋላ የቸምና ዘይት ለማምረት በብቸኛ ግብዓትነት እየተጠቀሙ ይገኛል፡፡

መሆኑም የቸምና ዘይት ከኑግ ብቻ የሚመረት በመሆኑ ለሰው ልጅ ጤና በጣም ተስማሚ መሆኑን በማከል፡፡

የአድማስ የገበሬዎች ህብረት ስራ ዩኒየን የግብይት ክፍል ኃላፊ አቶ አየለ ግርማ በበኩላቸው ዩኒየኑ በአዋጅ በተሰጠው ፈቃድ መሰረት የሚጠበቅበትን አገልግሎቶች እየሰጠ ይገኛል፡፡ እነዚህንም የአርሶ አደሩ ምርትና ምርታማነት ሊያሻሽሉ የሚችሉ የግብርና ግብዓቶች ማቅረብ፣ ትምህርት ስልጠናና የመጋዘን አገልግሎት መስጠት እንዲሁም ለአባል ማህበራቱ የብድር አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *