የአረፋ በዓል የአብሮነትና የመቻቻል ባህላችን የበለጠ የምናጎለብትበት ሊሆን እንደሚገባ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ሰርሞሎ ገለጹ።


የ2016 ዞናዊ የአረፋ በዓል ፌስቲቫል በጉራጌ ዞን ጌታ ወረዳ እድገት ቀበሌ በተለያዩ ዝግጅቶች በድምቀት ተከበረ።

የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ሰርሞሎ እንደገለፁት የአረፋ በአል በጉራጌ ብሄረሰብ ተራርቆ የቆየ ቤተሰብ በማገናኘት የተጣላ ካለ ይቅርታ የሚጠያየቅበት፣አብሮነቱንና መቻቻሉን የሚያጠናክርበት በአጠቃላይ ደስታው የሚገልጽበት ታላቅ በዓል መሆኑን አስረድተዋል።

በመሆኑም የአረፉ በአል አስተምህሮቱም የአብሮነትንና የመቻቻል ባህላችን የበለጠ እንድናጎለብት የሚያደርግ ስለሆነ ይህንን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባ ወ/ሮ ፋጤ ሰርሞሎ ገልጸዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በአረፋ በአል ሁሉም የብሄሩ ተወላጆች ከአራቱ ማዘናት ወደ አካባቢያቸው በመግባት በቤተሰባዊና በአካባቢው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ምን ይደረግ?ብሎ ከቤተሰቡና ከማህበረሰቡ ይመክራል።

በመሆኑም የአረፋ በዓል ከሃይማኖታዊ ይዘቱ በተጨማሪ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብራችን ይበልጥ የምናጠናክርበት ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል።

በበዓሉ ወቅት ያለው ለብቻው መብላት እንደሌለበት እና ከሚተርፈው ብቻ ሳይሆን ካለው ነገር የማካፈል ኃላፊነት የአለበት በመሆኑ የሰው ልጅ በመረዳዳትና በመደጋገፍ አብሮ መቆም እንዳለበት ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን አስገንዝበዋል።

የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ መሰረት አመርጋ እንደገለፁት የአረፋ በዓል ከሃይማኖታዊ ይዘቱ በተጨማሪ የጉራጌ ማህበረሰብ ሙስሊም ክርስቲያኑ የበለጠ እንዲተጋገዙ በማድረግ የአብሮነት እና የመቻቻል ባህላቸው የሚያነጸባርቁበት ታላቅ በዓል መሆኑ አስገንዝበዋል።

የጉራጌ ማህበረሰብ በርካታ አኩሪ እና የሀገር በቀል እውቀቶች ባለቤት ነው ያሉት ወ/ሮ መሰረት ለአብነትም የጉራጌ የቤት አሰራር፣ባህላዊ የዳኝነት ስርአት፣ጀፎረ፣እና የጉራጌ ክትፎ ተጠቃሽ ሲሆኑ እነዚህም በዩኒስኮ እንዲመዘገቡ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።

በዞኑ በርካታ አስደማሚ ባህላዊ፣ተፈጥሮአዊና ሰው ሰራሽ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች ያሉ በመሆኑ በመጎብኘትና በማስተዋወቅ ዘርፉን ማነቃቃት እንደሚገባ ኃላፊዋ መክረዋል።

የጌታ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ በህሩ ኸይረዲን እንደገለፁት የአረፋ በዓል አብሮነትን፣ፍቅርን መተሳሰብ፣ሰላምን እና መቻቻልን የሚያስተምረን በዓል ሲሆን ህብረተሰቡ ደግሞ አብሮ መስራት፣አብሮ መኖርና አብሮ መብላት ባህሉ ነው።

ይህ በመሆኑም በወረዳውም ህብረተሰቡ፣ባለሀብቱ፣የበጎ አድራጊዎች፣የተለያዩ የልማት ማህበራትና መንግስት በጋራ በመቀናጀት፣በመንገድ፣ በትምህርት ፣በመብራት፣በከተሞች መሰረተ ልማት እና በሌሎች የልማት ስራዎች ሲፊ እርብርብ እየተደረገ እንደሆነ ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ የመንገድ፣የመብራት፣በትምህርት በግብርና እና በሌሎችም ቀሪ ያለተሰሩ ስራዎች በመኖራቸው እነዚህም የህብረተሰቡ የመልካም አስተዳደር ችግር እየሆኑ በመሆኑ የሚመለከተው አካል እገዛ ማድረግ እንደሚገባ ጠይቀዋል።

የበዓሉ ታዳሚዎች እንዳሉት የአረፋ በአል ስናከብር የተቸገሩት በመርዳት፣የአብሮነትና የመቻቻል ባህላችን ይበልጥ ማጠናከርና በበዓሉ ወቅትም በአካባቢያዊ ጉዳዮች ላይ መወያየት ያስፈልጋል ብለዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *