የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር በመቅረፍ ህብረተሰቡ ተጠቃሚ ለማድረግ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ የደቡብ ክልል ውኃ መስኖና ማዕድን ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ መንግስት በጉራጌ ዞን ጉንችሬ ከተማ ከ 41 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚያስገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ አኖረ።

የክልሉ ውኃ መስኖና ማዕድን ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አክሊሉ አዳኝ እንዳሉት የጉንችሬ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት መሰረት ድንጋይ ባኖሩበት ወቅት እንደተናገሩት ውኃ ከመጠጥነት ባለፈ ለግብርና፣ ለከተማ ልማትና ለኢንቨስትመንት መስፋፋት የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ይገኛል።

በ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ለጉንችሬ ማህበረሰብ ቃል ከተገባለት ተግባራት አንዱ የንፁህ ውሃ አቅርቦት ማስፋፋት መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው የከተማው ህብረተሰብ የንጹህ መጠጥ ውሃ አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ የክልሉ መንግስት ከ41 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መመደቡን ገልጸዋል።

እንደ ኢንጂነር አክሊሉ ገለጻ የውኃ ግንባታው በስድስት ወራት ውስጥ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት እንዲችል የክልሉ መንግስት ክትትል የሚደርግ ሲሆን የውሃ ዝርጋታው የሚያልፍባቸው አካባቢዎች ከይገባኛል ነጻ እንዲሆኑ ህብረተሰቡ የድርሻውን አስተዋጽኦ ማበርከት ይጠበቅበታል ብለዋል።

በከተማው የሚገነባው የንጹህ መጠጥ ውኃ ፕሮጀክት ሲጠናቀቅ የከተማው እድገት ለማፋጠን ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወት ኃላፊው አስገንዝበዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድ ጀማል በበኩላቸው የውኃው መገንባት የአካባቢው የንጹህ የመጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ከመቅረፍ ባለፈ የከተማው እድገት ለማፋጠንና ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ብለዋል።

የከተማው ማህበረሰብ በመሰረታዊነት የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ችግር ለመቅረፍ የክልሉ መንግስት ላደረገው አስተዋጽኦ ምስጋናቸው አቅርበው ግንባታው ከተያዘለት ጊዜ አስቀድሞ እንዲጠናቀቅ ድጋፍና ክትትል ይደረግለታል ብለዋል።

በከተማው ከሚገነባው የንጹህ መጠጥ ፕሮጀክት ባሻገር ሌሎች መሰረተ ልማቶች በማስፋፋት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ መንግስት ከፍተኛ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝ አቶ መሀመድ አስረድተዋል።

በመሆኑም የከተማው እድገት ለማፋጠን ሁሉም ተቀናጅቶ መስራት ይጠበቅበታል ብለዋል።

አያይዘውም አቶ መሀመድ ህብረተሰቡን እያማረረ የሚገኘው የከተማው የአስፋልት መንገድ ግንባታ ውል በማቋረጥ ሁለተኛው ዙር ጨረታ ለማውጣት ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ ነው ብለዋል።

በከተማው የተጀመሩ የልማት ስራዎች በፍጥነት ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት እንዲችሉና የከተማው እድገት እንዲፋጠን ህብረተሰቡ በጋራ መቆም ይጠበቅበታል ብለዋል።

የጉንችሬ ከተማ ከንቲባ አቶ አብዱልቋድር ሂጂራ የከተማው ህብረተሰብ ተጠቃሚ ለማድረግ ከፍተኛ ገንዘብ በመመደብ የጌጠኛ ድንጋይ መንገድ፣ የመንገድ ዳር መብራት፣ ዲች እና አንድ ጥልቅ የውሃ ጉድጓድ እንዲሁም የውስጥ ለውስጥ መንገድ ከፈታና ግንባታ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።

ወይዘሮ ወርቅወት ልጋ፣ ፋናዬ ተስፋ እና አቶ ታየ ተረዳ የጉንችሬ ከተማ ነዋሪ ሲሆኑ በከተማው የነበረው ስር የሰደደ የውሃ ችግር በጤናቸው ላይ ከፍተኛ ጫና እንዳሳደረባቸው ገልጸዋል።

በከተማው የንጹህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት ባለመኖሩ ለውሃ ወለድ በሽታ ይዳረጉ እንደነበር አውስተው መንግስት የህብረተሰቡን አንገብጋቢ ችግር ለይቶ ለመፍታት የወሰደው እርምጃ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *