የንግዱ ማህበረሰብ አንድነቱ በማጠናከር የዞኑ ልማት ለማፋጠን የበኩሉን አስተዋጽኦ ሊያበረክት እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ።

የጉራጌ ዞን የንግድ ዘርፍ ማህበራት መስራች ጉባኤው በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።

የጉራጌ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ መላኩ ብርሃኔ በጉባኤው ላይ እንዳሉት ከጥንት ጀምሮ የጉራጌ ብሄረሰብ በታታሪ ሰራተኛነቱንና በንግድ ስራው የሚታወቀውን ያክል የንግድ ዘርፍ ማህበራት አደራጅቶ ከመንቀሳቀስ አንጻር ውስንነት ይስተዋልበታል።

የንግዱ ማህበረሰብ በማህበር መደራጀቱ መብቱ ለማስከበርና ግዴታውንም ለመወጣት እንዲሁም በሀገሪቱ በሚካሄዱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ በሚያደርገው ተሳትፎ ልክ ተገቢውን እውቅና እንዲያገኝ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ኃላፊው ገልጸዋል።

ዛሬ ምስረታውን ያካሄደው የንግድ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት በመስቀልና በአረፋ የጉራጌ ባህልና እሴት ሊያሳይ የሚችል ንግድና ባዛር በማዘጋጀት የቱሪስት መስህብ እንዲሆን በማድረግ ከዘርፉ በሚገኘው ገቢ የዞኑ ልማት ለማፋጠን በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።

አክለውም በሀገሪቱ የተከሰተውን የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለውን የሰንበት ገበያ በሁሉም አካባቢዎች እንዲጠናከር የንግድ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤቱ ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባ አቶ መላኩ አስገንዝበዋል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የንግድ ዘርፍ ማህበራት ምክር ቤት መመስረቱ በመንግስትና በንግዱ ማህበረሰብ መካከል መልካም ግንኙነት እንዲኖር የሚያስችል ነው ሲሉ ተናግረዋል።

የንግዱ ማህበረሰብ በሀገሪቱ በሚከናወኑ ማህበራዊ፣ ፓለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ንቁ ተሳትፎ በማድረግ የራሱን አሻራ በጉልህ ለማሳረፍ ይረዳል ብለዋል።

የምስረታ ጉባኤው 11 አባላት ያሉት የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በመምረጥ መጠናቀቁን የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *