የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት የተጀማመሩ ስራዎችን በማጠናከር የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባ የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ።


የጉራጌ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ የ9 ወራት እና የ2ኛ ዙር የመቶ ቀን እቅድ አፈጻጸም መነሻ ያደረገ የውይይት መድረክ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።

የጉራጌ ዞን አስተዳደር ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ፈቀደ በመድረኩ ተገኝተው እንዳሉት በህገወጥ መልኩ የምርት ክምችት በሚያደርጉ ነጋዴዎች ላይ የክትትልና የቁጥጥር ስራ በማጠናከር ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ በቅንጅት ሊሰራበት ይገባል።

አሁን ላይ ያለው የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት በዞኑ የሰንበት ገበያ ከማጠናከር ባለፈ አምራቹ ከሸማቹ በቀጥታ ለማገናኘት አቅርቦት ላይ በትኩረት ሊሰራበት እንደሚገባም ተናግረዋል።

የጉራጌ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ መላኩ ብርሃኔ በመክፈቻ ንግግራቸው እንዳሉት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በዞኑ የተጀማመሩ የሰንበት ገበያ ከማጠናከር ጎን ለጎን የገበያ ትስስር መፍጠር ይገባል።

ከዚህም ባለፈ ህገወጥ የምርት ክምችት ለመከላከልና ለመቆጣጠር የንግድ ቁጥር ስራ በትኩረት መስራት ይገባል ያሉት አቶ መላኩ የነዳጅ ማደያ ላይ ያለው ህገወጥነት ማስተካከል ላይ መሰራት እንዳለበት ጠቁመዋል።

በዞኑ ከ11 ሺህ በላይ ንግድ ምዝገባና ፈቃድ በማደስ በዚህም ከ1ነጥብ 8 ሚሊዮን በላይ ሀብት የመሰብሰብ ስራ ተሰርቷል።

በዞኑ የንግድ ዘርፍ ማህበራትና የነጋዴዎች ጥምረት የማቋቋም ስራ መሰራቱንም ገልጸዋል።

በህገወጥ መንገድ ሲነግዱና እህል በማከማቸትና በሌሎችም ቅጣት የተገኘ 7 ሚሊዮን 335 ሺህ 445 ብር በመሰብሰብ ለመንግስት ገቢ መደረጉንም አመላክተዋል።

በአንዳንድ አካባቢዎች የተጀማመሩ ህገወጥ ንግድን ለመቆጣጠርና አምራችና ሸማቹ በቀጥታ በማገናኘት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተሰሩ ስራዎች አበረታች መሆናቸውን ያነሱት ኃላፊው ይህ ተግባር በቀጣይ አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ገልጸዋል።

በዞኑ 12ሺህ 950 ህገወጥ ቤንዚል በመውረስ ለመንግስት ገቢ መደረጉንም ተናግረዋል።

ተሳታፊዎች እንዳሉት የኑሮ ውድነት ለማረጋጋት የገበያ ትስስር ከመፍጠር ባለፈ ህገወጥነትን ለመከላከል ከባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅቶ መስራት ይኖርበታል ብለዋል።

አክለውም የሰንበት ገበያ ከማጠናከር ባለፈ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በኢንቨስትመንት፣ በተደራጁ ወጣቶች የመረቱና ሌሎችም ምርቶችን ወደ ሸማቹ ማቅረብ ይገባል ብለዋል።

በተግባር አፈጻጸም ወቅት የነበሩ ጠንካራ ጎኖች በማጠናከርና በቀጣይ ውስንነቶች በማረም በትኩረት እንደሚሰሩም ተናግረዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *