የትምህርት ጥራት የበለጠ ለማሻሻልና ወቅቱን የሚመጥን ተግባር ለማከናወን ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት እንደሆነ የጉራጌ ዞን ትምህርት መምርያ አስታወቀ።

መምሪያው የ2014 ትምህርት ዘመን በወረዳና ከተማ አስተዳደሮች በሚገኙ ትምህርት ቤቶች የተደረገው የመጀመሪያ ዙር መደበኛ ሱፐርቪዥን ሪፖርት ማጠቃለያ መድረክ በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ አቶ አስከብር ወልዴ እንዳሉት የትምህርት ጥራት የበለጠ ለማሻሻልና ወቅቱን የሚመጥን ተግባር ለማከናወን ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራበት መሆኑን አሳውቀዋል።

በሱፐርቭዢን ወቅት የተለዩ ጠንካራ ጎኖች እና መሻሻል ያለባቸዉ ጉዳዮች በመለየት የትምህርት ማረጋገጫ ፓኬጅ አፈጻጸም በለፉት ወራት ታቅደዉ ያልተካናወኑ ዋና ዋና ግቦችን ለይቶ እንዱፈፀሙ መክረዋል።

ተግባር ተኮር ጎልማሶች ትምህርት በማጠናከር፣ለቅድመ መደበኛ ትምህርት ትኩረት ሰጥቶ በበጀት በመደገፍ ፣የመምህራን አቅም ግንባታ ስልጠናዎች እንዲሁም ማንኛዉም የመልካም አስተዳደር ችግሮች በዕቅድ መፍታት እና መፈጸም እንዳለበት አመላክቷል።

ተከታታይ የሆነ ድጋፍ እና ክትትል መደረጉ በየትምህርት መዋቅሮች ላይ መነቃቃት ከመፍጠሩ በተጨማሪ የሰዉ ኃይል እጥረትን ለመቅረፍ፣የተማሪ ዉጤት እና ስነምግባር ለማሻሻል፣ ማህበረሰብ፤የአከባቢ ተወላጆች እና ባለሀብቶችን ለማስተባበር ጉልህ ሚና ተጫውቷል ብለዋል።

የጎልማሶች ትምህርት አሰጣጥ አናሳ መሆኑ፣ በውስን ትምህርት ቤቶች የትምህርት ብክነት መኖሩ፣የፕላዝማና የሬድዮ ትምህርት መቆራረጥ፣የመምህራንና የመጽሀፍት እጥረት ከገጥሙ ችግሮች ለአብነት የሚጠቀሱ እንደሆኑና በቀጣይ ሊፈቱ እንደሚገባ አሳስበዋል ።

በቀጣይም የማጠናከሪያ ትምህርቶች በመስጠት፣የቅድመ አንደኛ ትምህርት መስጫ ጣቢያዎች ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ እና የወላጆች፣የተማሪዎችና የመምህራን መድረኮች መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ አቅጣጫ ተቀምጧል ተብሏል።

ተማሪዎች የፈጠራ ክህሎታቸው እንዲዳብር በሳይንስና ቴክኖሎጂ ትምህርቶች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባም ተገልጿል።

አቶ መሀመድ ሀሰን አቶ ታደለ ብርሀኔ አለማየሁ ኬኔ የወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊዎች ሲሆኑ የትምህርት ጥራት ለማምጣት የተማሪ ወላጆች ፣ባለሀብቶች እና ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት እየሰራንበት ነው ብለዋል።

አክለውም ከዚህ በፊት የተማሪዎች ስነ-ምግባር ግድፈት የጎልማሶች ትምህርት መቀዛቀዝ የመምህራን እጥረትና በተወሰኑ ትምህርት ቤቶች የመጽሀፍት አለመሟላት ለትምህርት ስራው ተግዳሮት እየሆኑ መሆናቸው አመላክተዋል።

በሴክተሩ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመለየት፣ በማረምና በተግባር በመገምገም እንዲሁም ለዘርፉ ትኩረት በመሰጠት ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች ታይቷል ነው ያሉት።

ለቀጣይም በተሰጣቸው ግብረመልስ መሰረት ጠንካራውን በማስቀጠል ችግሩን ለመቅረፍ ተግተን እንሰራለን ብለዋል

በመጨረሻም በቀጣይ 6 ወራት የተማሪዎች ውጤት እንዲሻሻል በሚደረጉ ተግባራት ላይ የውል ስምምነት በመፈራረም ፕሮግራሙ ተጠናቋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *