የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥና የተማሪዎች ዉጤት ለማሻሻል የመምህራንና የሌሎችም ባለድርሻ አካላት ሚና የጎላ እንደሆነም የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ አስታወቁ።

ለመምህራን ፣ ለርዕሰ መምህራንና ለሱፐርቫይዘሮች ሲሰጥ የነበረዉን የአዲሱ ስርአተ ትምህርት ስልጠና ማጠቃለያ የዞኑ ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች የተለያዩ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደር ተዛዙረዉ ምልከታ አድርገዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ እንዳሉት የመምህራን አቅም ለመገንባት መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰረ ይገኛል።

በዞኑ በሁሉም አካባቢዎች ለመምህራን እየተሰጠ ያለዉን የአዲሱ ስርአተ ትምህርት ስልጠና ለትምህርት ጥራትና ለተማሪዎች ዉጤት መሻሻል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረዉም አሰታዉቀዋል።

ባለፉት 30 አመታት በትምህርት ስርአት በጣም ከፍተኛ ችግር የነበረበት እንደነበረም አስታዉሰዉ በ2014 ዓመተ ምህረት የ12ኛ ማትሪክ ፈተና ከኩረጃ ሙሉ ለሙሉ ነጻ በሆነ መልኩ በዩኒቨርሲቲዎች ገብተዉ እንዲፈተኑ ተደርጎ ዉጤቱ የትምህርት ገበናችንን ያጋለጠ እንደሆነም አስታዉሰዋል።

ከተፈተኑ ተማሪዎች በሙሉ ከ96 ከመቶ በላይ ተማሪዎች መዉደቃቸዉና ዉጤት እንዳላመጡም አመላክተዉ ይህም እንደ ሀገር አቀፍ አስደንጋጭ በመሆኑም የትምህርት ስርአትና ፖሊሲዉን በመቀየር እአዲስ ስርአተ ትምህርተ ተቀርጾ የመማር ማስተማር ስራዉ እየተሰጠ እንደሆነም አብራርተዋል።

ትዉልድን በእዉቀትና በስነ ምግባር በመቅረጽ ሀገርን መገንባት ያሰፈልጋል ያሉት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ የአዲሱ ስርአተ ትምህርት ስልጠና መጀመሪያዉ ዙር በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ የአሰልጣኞች ስልጠና መሰጠቱም አስረድተዉ ለሁለተኛ ዙር ሁሉም የሀይስኩል መምህራን በክላስተር በመሆን ስልጠና ሲከታተሉም እንደነበረና ስልጠናዉ በዛሬዉ እለት አጠናቀዋል ብለዋል።

ከአምና ጀምሮ በትምህርት ዘርፍ ሰፊ ስራዎችና የትምህርት ንቅናቄ ስራዎች መሰራቱንም እንዲሁም የትምህርት ቤቶች ደረጃዎች ለማሻሻል በተሰራዉ ስራ በዚህም የላይብሪና የላብራቶሪ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ የትምህርት ቁሳቁሶችና የመማሪያ ክፍሎች የማስፋፋት ስራ መላዉ የዞኑ ህዝብ በማሳተፍ ሞዴል የሚባል ስራ መሰራቱም ተናግረዋል።

የመጻፍት አቅርቦት ላይ መንግስት ከፍተኛ ወጪ በማዉጣት ከ9 እስከ 12ኛ ክፍል በሀገር አቀፍ ደረጃ ትምህርት ሚኒስቴር ሀላፊነት ወስዶ በአብዛኛዉ ትምህርት ቤቶች መዳረሱም ተናግረዉ የ7ኛ እና የ8ኛ ክፍል የመማሪያ መጽሀፍት ክልሉ አዘጋጅቶ አቅርቧል ብለዉ ለአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች መጽሀፍት ተደራሽ ለማድረግ ባለሀብት ፣አርሶአደርና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍሎች እንዲሳተፉ ለማድረግ የንቀናቄ መድረኮች ተጀምሯል ብለዋል።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ሀላፊ አቶ መብራቴ ወልደማሪያም እንዳሉት በዞኑ በተለያዩ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች ከትላንት ጀምሮ ለትምህርት ባለድርሻ አካላት ሲሰጥ የነበረዉ አዲሱ ሰርዐተ ትምህርት ትውውቅ እና ሌሎችም የተሰጡ ስልጠናዎች በመማር ማስተማሩ ላይ ተጨባጭ ለውጥ የሚያመጣ ነዉ።

በአዲሱ የስርዐተ ትምህርት ይዘቶች፣በፈተና አዘገጃጀትና በክፍል ውስጥ መማር ማስተማር አመራር ላይ ለሁለት ተከታታይ ቀናት ከ1 ሺህ 2 መቶ 69 በላይ ለሆኑ መምህራንና ርዕሰ መምህራን ሲሰጥ የነበረው የስልጠና በሁሉም ብታ በስኬት ተጠናቋል ብለዋል።

የመምህራን አቅም በስልጠና እንዲታገዝ በማድረግ በትምህርት ጥራትና በተማሪዎች ዉጤት መሻሻል ላይ ተጨባጭ ዉጤት ማምጣት እንደሚያስችልም አመላክተዉ ሰልጣኝ መምህራኖች በቆይታቸዉ ያገኙትን እዉቀት ተጠቅመዉ በዞኑ የገጠመዉን የዉጤት ስብራት በቅንጅት በመስራት ማቃናት እንዳለባቸዉም ገልፀዋል።

አቶ መብራቴ አክለውም ለስልጠናው መሳካት ቀድሞ ከዞን ጀምሮ በየደረጃው ሰፊ ዝግጅቶች መደረጋቸው ገልፀው ለስልጠናው መሳካት ከፍተኛ እገዛ ላደረጉ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ አመራርና ባለሙያዎች ጀምሮ በየደረጃው ላለው የፖለቲካና የትምህርት አመራር እንዲሁም ባሙያዎች ሁሉ ምስጋናቸው አቅርበዋል።

የጉራጌ ዞን መምህራን ማህበር ሰብሳቢ አቶ ደረጄ እስጢፋኖስ በበኩላቸዉ በሁሉም አካባቢዎች ለመምህራን ሲሰጥ የነበረዉ የአዲሱ ስርአተ ትምህርት ስልጠና በተማሪዎች ዉጤትና ስነ ምግባር ላይ ተጨባጭ ዉጤት የሚያመጣም እንደሆነም አመላክተዋል።

መምህራን የስርዐተ ትምህርት ስልጠና በቀጥታ ከመደበኛ ስራዎቻቸዉ ጋር የሚገናኝ በመሆኑ ከሌሎች የስለጠናዎች በተለየ መልኩ በከፍተኛ መነቃቃትና ስሜት ተከታትለዋል።

ስልጠናዉ ትኩረት ያደረገዉ የተማሪዎች የፈተና አዘገጃጀት ፣በክፍሉ ዉስጥ የመማር ማስተማር አመራሩን የሚመለከት ስለሆነ ሰልጣኞች በልዩ ትኩረት ተከታትለዉ ዛሬ አጠናቀዋል ብለዋል ሲል የዘገበዉ የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ነዉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *