የትምህርት ቤቶች ደረጃና የተማሪዎች ውጤት ለማሻሻል በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ፡፡


በእንደጋኝ ወረዳ የማራቢቾ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ደረጃ ለማሻሻል የገቢ መሰብሰቢያ መርሃ ግብርና የመሰረት ድንጋይ በጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ በአቶ ላጫ ጋሩማ ተቀምጧል፡፡

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በፕሮግራሙ ላይ እንዳሉት ትምህርት የአንድን አካባቢ መለወጫ ቁልፍ መሳሪ መሆኑን በመገንዘብ የትምህርት ቤቱ የቀድሞ ተማሪዎች ህብረት የአካባቢው ማህበረሰብና ባለሀብቶች በማስተባበር የማራቢቾ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ደረጃ ለማሻሻል እየተደረገ ያለው ጥረት አበረታች ነው፡፡

በሀገሪቱ የትምህርት ተደራሽነት ለማረጋገጥ በተሰራው ልክ ጥራት ለማስጠበቅ የተሰራው ስራ አነስተኛ ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው ይህንን ችግር ለመቅረፍ ትምህርት ቤቶች መሰረተ ልማት በማሟላት ደረጃቸውን በማሻሻል የተማሪዎች ውጤት እንዲያሳድጉ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡

በዚህ ዓመት ከ400 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የትምርት ቤቶች ደረጃ ለማሻሻል ስራ ላይ እንደዋለ የገለጹት አቶ ላጫ ጋሩማ በሚቀጥሉት 3 ዓመታት በዞኑ የሚገኙ ሁሉም ትምህርት ቤቶች ደረጃቸው ለማሻሻል ይሰራል፡፡

በተያያዘ የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ ግብዓት የማሟላት ስራ ትኩረት ሰጥቶ ሊሰራ እንደሚገባ ያብራሩት ዋና አስተዳዳሪ ይህንንም እውን ለማድረግ በመንግስትና በህብረተሰብ ተሳትፎ ከ78 ሚሊዮን ብር በላይ በፈጀ ወጪ ከ1 እስከ 6 ክፍል ለሚማሩ ተማሪዎች መጽሐፍ በማሳተም ተደራሽ ማድረግ ተችሏል፡፡

የትምህርት ቤቱ ደረጃ ለማሻሻል የሚያስችል ገቢ ለመስብሰብ የተጀመረው ስራ አጠናክሮ በማስቀጠል በአጭር ጊዜ ግንባታው ተጠናቆ ለምረቃ መብቃት እንዳለበት እና እንደ ዞን አስተዳደር ለመንገድና ለሌሎች የአካባቢው ልማት የተለየ ድጋፍ እንደሚደረግ አቶ ላጫ ጋሩማ ገልጸዋል፡፡

የእንደጋኝ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙሉቀን ገዙ በበኩላቸው በወረዳው በህብረተሰብ ተሳትፎ የመንገድ ግንባታ፣ የትምህርት ግብዓት ማሟላት፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ለማሻሻል እንዲሁም ሌሎች የማህበረሰቡ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ተናግረዋል፡፡

ይሁን እንጂ በወረዳው ከፍተኛ የመንገድ ልማት፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት፣ የሆስፒታል ግንባታ እንዲሁም የመብራት ተደራሽነት ችግሮች የህብረተሰቡ የዘወትር የልማት ጥያቄ በመሆናቸው የዞኑ አስተዳደር በዕቅድ ምላሽ ሊሰጥ ይገባል ሲሉ አቶ ሙሉቀን ጠይቀዋል፡፡

የማራቢቾ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት በ1950 ዓመተ ምረት በዛፍ ስር የመማር ማስተማር ስራ በመጀመር በርካታ ምሁራን ያፈራ ሲሆን የት/ቤቱ የቀድሞ ተማሪዎች ህብረት ሀሳብ አመጪነት ደረጃውን ለማሻሻል በ121 ሚሊዮን ብር ግንባታ ለማካሄድ በዞኑ ዋና አስተዳዳሪ በአቶ ላጫ ጋሩማ የመሰረት ድንጋይ መቀመጡን ጠቁመዋል፡፡

የማራቢቾ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት የቀድሞ ተማሪዎች ህብረት ሰብሳቢ አቶ አገዘ ገ/መድህን በዚህ ወቅት እንደተናገሩት ትምህርት የልማት ሁሉ መሰረት ነው የሚባለው የሰው አይምሮ ስለሚቀይር ነው፡፡

ይህንን የተገነዘቡ የማራቢቾ ት/ቤት የቀድሞ ተማሪች በመደራጀት ህብረት ፈጥረው ዘላቂነት ባለው መልኩ የትምህርት ቤቱ ደረጃ ለማሻሻል የሚያስችሉ ግንባታዎችና መሰረተ ልማቶች ለማሟላት ከፍተኛ እንቅስቃሴ በማድረግ ላይ መሆናቸውን አቶ አገዘ ገልጸዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *