የትምህርት መሰረተ ልማትና ግብአት ማሟላት በሀገር አቀፍ ደረጃ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት ሚናው የላቀ መሆኑን የኢፌድሪ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ገለጹ።


በጉራጌ ዞን እንደጋኝ ወረዳ በምስጋናው የበጎ አድራጎት ድርጅት የሚገነባው የጀዳ አንደኛና መለስተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ተቀመጠ።

የኢፌድሪ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ዴኤታ ክቡር አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ እንደገለጹት የትምህርት መሰረተ ልማትና ግብአት ማሟላት በሀገር አቀፍ ደረጃ ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ለማፍራት ሚናው ትልቅ ነው።

ትምህርት ቤት መገንባት ብቻ ግብ አለመሆኑን ያነሱት አምባሳደሩ በስነምግባር የታነጸ ትውልድ ለማፍራት ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት በመላክ ማስተማር ይኖርባቸዋል።

የትምህርት ቤቱ ግንባታ በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ እንደሚሰራ አምባሳደር ምስጋናው አርጋ ገልጸዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ልዩ አማካሪ አቶ ዳርጌ ተክሉ እንዳሉት በባለፉት አመታት በሀገር ደረጃ የትምህርት ሽፋንና ጥራት ለማረጋገጥ በመንግስት፣ በህዝብና በበጎአድራጎት ድርጅት በርካታ ጥረቶች በማድረግ አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል።

እንደ ሀገር ብሎም በዞኑ አብዛኛው ትምህርት ቤቶች ደረጃቸውን የጠበቁ ባለመሆናቸው የትምህርት ጥራት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩን ጠቁመው በዛሬው እለት በወረዳው በክቡር አምባሳደር ምስጋናው የበጎ አድራጎት ድርጅት የሚገነባው ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ቤት የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት አስተዋጽኦው የላቀ መሆኑን ገልጸዋል።

ፕሮጀክቱ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ባለሀብቶች፣ የቀበሌው ነዋሪዎች የበኩላቸውን ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀው የዞኑ መንግስትም አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርግ አመላክተዋል።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወልደማርያም በዞኑ ከሚገኙ 401 አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 82 በመቶ ከደረጃ በታች መሆናቸውን ጠቅሰው የጀዳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤትም አንዱ እንደነበር እንስተዋል።

በሀገር ደረጃ ትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ ተከትሎ በዞኑ በበጀት አመቱ መንግስትና ማህበረሰቡ በመቀናጀት ከ490 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የተለያዩ ግንባታዎችና ግብአት የማሟላት ስራ ተሰርቷል ብለዋል።

የትምህርት ስብራት ለመጠገንና የተማሪዎች ስነምግባርና ውጤት ለማሻሻል በሚደረገው ጥረት የምስጋናው አርጋ ፋውንዴሽን ታሪክ የማይረሳው ትውልድ የሚጠቅም ትልቅ ስራ እየሰሩ በመሆኑ አመስግነዋል።

የእንደጋኝ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሙሉቀን ገዙ በወረዳው ካሉ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውስጥ አብዛኛዎቹ ከደረጃ በታች በመሆናቸው ያሉባቸውን የመሰረተ ልማትና የግብአት ችግር ለመቅረፍ ማህበረሰቡ በማስተባበር በርካታ ስራዎች እየተሰራ ይገኛል።

በዛሬው እለት በምስጋናው አርጋ የበጎ አድራጎት ድርጅት የጀዳ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ደረጃውን በጠበቀ መልኩ ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ በማኖራቸው አመስግነው ፕሮጀክቱ እውን እንዲሆን የወረዳው መንግስትንና ማህበረሰቡ የበኩሉን እገዛ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።

በአካባቢው አግኝተን ያነጋገራቸው ነዋሪዎች እንዳሉት የምስጋናው አርጋ የበጎ አድራጎት ድርጅት የትምህርት ቤቱ ችግር በመረዳት ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ቤት ለመገንባት የመሰረት ድንጋይ በማኖራቸው ደስተኛ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ፕሮጀክቱ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ የአካባቢው ነዋሪዎች አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

በእለቱም ትምህርት ቤቱ አሁናዊ ያለበት ደረጃ ተዟዙረው ተመልክተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *