የታዳሽ ሀይል አማራጭን በመጠቀም በሁሉም የሀገሪቱ ገጠራማ አካባቢዎች ዜጎችን የሞባይል ኔትወርክ ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን የኢትዮ ቴሌኮም ኩባንያ አስታወቀ።

ኩባንያው በጉራጌ ዞን እዣ ወረዳ ቦዠባር ከተማ አስተዳደር ያስገነባውን የገጠር ሞባይል ኔትወርክ ሶሉሽን ፕሮጀክትን ሥራ አስጀምሯል።

በኢትዮ ቴሌኮም የኔትወርክ ኢንፍራስትራክቸር ምክትል ቺፍ ኦፊሰር አቶ ዓለም ኃይለማርያም እንደገለጹት፣ የገጠር ሞባይል ኔትወርክ ሶሉሽን አገልግሎት ሁሉም የሀገሪቱ ዜጎች ከሞባይል ኔትወርክ ተጠቃሚ እንዲሆን የሚያስችል ነው።

ፕሮጀክቱ ራቅ ያሉና ገጠራማ በሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች፣ የመሬት አቀማመጥ ምቹ ያልሆነባቸው እንዲሁም የመንገድ መሰረተ ልማት ያልተዳረሰባቸው አካባቢዎች ዜጎች የሞባይል የኔትወርክ በቀላሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ የሚያስችል ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት ተደራሽ ባልሆነባቸው አካባቢዎች በፀሐይ ኃይል የሚሰራ የሞባይል ኔትወርክ ታዎር በመዘርጋት ህብረተሰቡን የኔትወርክ ተጠቃሚ የሚያደርግ መሆኑንም አስረድተዋል።

ይህም ተቋሙ ማህበረሰቡን በኔትወርክ ለማገናኘት የያዘውን ተልዕኮ ለማሳካት ያግዛል ብለዋል።

በገጠር ሞባይል ኔትወርክ ሶሉሽን አገልግሎት በ305 የገጠር ቀበሌያት ከ900 ሺህ በላይ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ተናግረዋል።

የታዳሽ ሃይል አማራጭን በመጠቀም ሁሉንም የሀገሪቱ ዜጎች በሞባይል ኔትወርክ ለማገናኘት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑንም አቶ ዓለም አስረድተዋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ በበኩላቸው እንዳሉት ዲጂታል ኢኮኖሚን ተግባራዊ በማድረግ ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ ወቅቱን የሚመጥን አሰራር መከተል ይገባል።

ኢትዮ ቴሌኮም በዞኑ በመሰረተ ልማት እጥረት የቴሌኮም አገልግሎት ተደራሽ ያልሆነበትን የቦዠባር ከተማንና አካባባውን ማህበረሰብ በኔትወርክ ተጠቃሚ ማድረጉን ገልጸዋል።

ኢትዮ ቴሌኮም በገጠር ሞባይል ኔትወርክ ሶሉሽን ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የጀመረውን ተግባር በሌሎችም የዞኑ አካባቢዎች እንዲያስፋፋ ጠይቀዋል።

የቦዠባር ከተማ ነዋሪ ወይዘሮ ሰሚራ ኑርሰማ በበኩላቸው የዲጂታል ቴክኖሎጂ ትግበራ ጊዜ፣ ጉልበትና ገንዘብን በመቆጠብ በጎ አስተዋጾ እንዳለው ገልጸዋል።

ከዚህ ቀደም በአካባቢያቸው የሞባይል ኔትወርክ በቀላሉ ስለማይገኝ አምቡላንስ ጠርቶ ወላድ እናቶችን ወደ ጤና ተቋም ለማድረስ ባለመቻላቸው ለጉዳትና ሞት የሚጋለጡበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰዋል።

የሞባይል ኔትወርክ ለማግኘት ከ25 ኪሎ ሜትር በላይ ለመጓዝ ይገደዱ እንደነበር አስታውሰው፣ የኔትወርክ አቅርቦቱ ይህን ችግራቸውን እንደሚፈታ ተናግረዋል።

በአገሪቱ የተለያዩ አካባዎች ለመጀመሪያ ጊዜ አገልግሎት መስጠት የጀመሩት የገጠር የሞባይል ኔትወርክ ሶሉሽኖች የኤሌክትሪክ ሀይል በሌለባቸው አካባቢዎች የተተከሉ ናቸው።

ከዚህ ቀደም ምንም ዓይነት የቴሌኮም አገልግሎት ባላገኙ አካባቢዎች ላይ የተተከሉ ሲሆን የራሳቸው ሶላር የኃይል አቅርቦት ያላቸው መሆኑም ታውቋል።

በፕሮጀክቱ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ላይ የኢትዮ ቴሌኮም እና የጉራጌ ዞን ከፍተኛ አመራሮችና የአካባው ነዋሪዎች ተገኝተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *