የታክስ ስወራን ለመከላከል የኢንተለጀንስና የቁጥጥር ስራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል በገቢ ዘርፍ የሚፈለገዉን ዉጤት ማምጣት እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ።

መስከረም 10/2015 ዓ.ም

የታክስ ስወራን ለመከላከል የኢንተለጀንስና የቁጥጥር ስራዎችን አጠናክሮ በማስቀጠል በገቢ ዘርፍ የሚፈለገዉን ዉጤት ማምጣት እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ገቢዎች መምሪያ አስታወቀ።

በዞኑ በተያዘው በጀት አመት ከ2 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ እየተሰራ መሆኑ ተገለጸ።

የመስቀል በአል ምክንያት በማድረግ ወደ ዞናችን የሚመጡ እንግዶችና ሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች የእቃ ግዢ ወይም ሌሎች አገልግሎቶች ሲያገኙ ደረሰኝ መጠየቅና መቀበል እንዳለባቸዉም ጥሪ ተላልፏል።

ለአንድ ሀገር ኢኮኖሚያዊ እድገት እንዲሁም ሀገራዊ ለዉጡን በዘላቂነት ለማረጋገጥ የግብር ከፋዩ ማህበረሰብ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ በዞናችን የሚገኙ ግብር ከፋዮች በሙሉ የግብር/ታክስ ግዴታውን በአግባቡ በመወጣት ሀገራዊ ግዴታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል።

የጉራጌ ዞን ገቢዎች መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙራድ ረሻድ እንዳሉት በዞኑ በሁሉም አካባቢዎች ኢኮኖሚዉ ያመነጨዉን ገቢ በተገቢዉ ለመሰብሰብ ከመቼዉም ጊዜ በላይ በትኩረት እየተሰራበት ነዉ።

በዞኑ 25 ሺህ 7 መቶ 67 የደረጃ “ሐ” ግብር ካፋዮች፣ 9መቶ 49 የደረጃ ለ ግብር ከፋዮች እንዲሁም 1 ሺህ 5 መቶ 8 የደረጃ “ሀ” ግብር ከፋዮች እንደሚገኙም አስረድተዋል።

በአጠቃላይ በሶስቱም የግብር ከፋዮች ደረጃዎች ከአንድ መቶ ሚሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ እስካሁን ድረስ የደረጃ ሐ እና ለ ግብር ከፋዮች የግብር ግዴታቸዉን የተወጡ ሲሆን የእቅዳችንን 100% መፈፀም ተችሏል። ይህም ካለፉት አመታት ጋር ሲነጻጸር የተሻለ እንደሆነም ተናግረዋል።

ባለፉት ሁለት ወራት ከደረጃ ” ሐ” ግብር ከፋዮች 72 ሚሊየን 7 መቶ 56 ሺህ ብር ፣ ከደረጃ ” ለ” 7 ሚሊየን 9 መቶ 96 ሺህ 2 መቶ 33 ብር መሰብሰብ እንደቻሉም ያስረዱት አቶ ሙራድ ከደረጃ “ሀ” ከ24 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ እየሰሩ እንደሆነም አመላክተዋል።

ባለፈዉ በጀት አመት ከ1 ነጥብ 8 ቢሊየን ብር በላይ ለመሰብሰብ እቅድ ተይዞ ከ1 ነጥብ 94 ቢሊየን ብር በላይ በመሰብሰብ ከ100% በላይ ማሳካት መቻሉም አስታዉሰዋል።

በተያዘዉ በጀት አመት በዞኑ በሁሉም ወረዳዎችና ከተማ አስተዳድሮች ከ2 ነጥብ 3 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ ለመሰብሰብ እቅድ ታቅዶ ከፍተኛ ርብርብ እየተደረገ እንደሆነም አስረድተዉ በሁለት ወር ዉስጥ ከ285 ሚሊየን 863 ሺህ ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻላቸዉም ተናግረዋል።

በዘንድሮ በጀት አመት የያዙትን ዕቅድ ሙሉ ለሙሉ ማሳካት እንዲቻል ሰፊ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ በመጥቀስ የደረጃ “ሀ” ግብር ከፋዮች እስከ ጥቅምት 30 ድረስ ሒሳባቸውን አሳውቀው እንዲከፍሉ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በዞናችን ዘንድሮ በርካታ ፈተናዎች እንዳሉና ግብር ከፋዩ ማህበረሰብ በተነሳሽነትና በቁርጠኝነት ለየትኛዉም አጀንዳ ሳይንበረከክ ግብር የመክፈል ግዴታዉን እየተወጣ ያለበት ሁኔታዎችን መኖሩም ጠቁመዋል።

በተለያዩ የማስተማሪያ ዘዴዎች ለግብር ከፋዩ ማህበረሰበ የፊት ለፊት የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራ በመስራት፣ የጋራ መድረኮች በማዘጋጀት፣ በወልቂጤ ኤፍ ኤም ሬድዮ የአየር ሰአት በመግዛት ፤ በብሮሸርና በማህበራዊ ሚዲያ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ በስፋት እየተሰራ እንደሆነም አብራርተዋል።

በተጨማሪም የታክስ ስወራ እና ማጭበርበር ስራዎችን ለመቀነስ የክትትል ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን እና የታክስ ህጉን በማያከብሩ ግብር ከፋዮች ላይ አስተዳደራዊ እና ህጋዊ እርምጃዎችን የመውሰድ ስራዎችም እየተሰሩ መሆኑን አብራርተዋል።

በመጨረሻም መጪዉን የመስቀል በአል ለማክበር ወደ አገር ቤትና ወደ ተለያዩ አካባቢዎች የሚገቡ የህብረተሰብ ክፍሎች የእቃ ግዢ ወይም ሌሎች አገልግሎቶች ሲያገኙ ደረሰኝ መጠየቅና መቀበል እንዳለባቸዉም ጥሪ አስተላልፈዋል።

በወልቂጤ ከተማ የሰኪና የሙስሊም ስጋ ቤት ባለቤት አቶ ሱልጣን ይርጋለም ግብር በወቅቱ በመክፈልና ደረሰኝ በተገቢዉ ለተገልጋዮ ማህበረሰብ እየሰጡ እንደሆነም ተናግረዋል።

መንግስት በሚሰበስበዉ ገቢ የአካባቢዉ ልማት ላይ ተጨባጭ ለዉጥ ማምጣት እንዳለበትም አስረድተዉ ማህበረሰቡ ግብር መክፈል ግዴታዉ እንደሆነም ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራዉ በስፋት ሊሰራበት እንደሚገባም አብራርተዋል ሲል የዘገበዉ የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ነዉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *