የተቀናጀ የግብርና ልማት ስራ አጠናክረው በመስራታቸው ውጤታማ መሆናቸውን በጉራጌ ዞን የጉመር ወረዳ የበሽመንዳ እርሻ ልማት ባለቤት አቶ ሀሺም ጀማል ተናገሩ፡፡


በዞኑ በፍራፍሬ ዘርፍ በትኩረት በመስራት የህብረተሰቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነታቸውን ይበልጥ ለማረጋገጥ እየሰራ እንደሚገኝ የጉራጌ ዞን ግብርና መምሪያ ገለጸ።

የበሽመንዳ የግብርና ልማት ድርጅት ባለቤት አቶ ሀሺም ጀማል እንዳሉት እርሻ ልማቱ በ2ሺ አመተ ምህረት የጀመሩት ሲሆን የደጋ አፕል፣ ፕሪም፣ ከብቶችንና በጎችን ከማርባት ባለፈ ምርጥ ዘር በማባዛት በትኩረት እየሰሩ ይገኛሉ።

የተቀናጀ የግብርና ልማት ስራ በትኩረት በመስራታቸው ውጤታማ እንደሆኑ ያነሱት አቶ ሀሺም ያመረቱት ምርት ወደ ገበያ በማውጣት ይበልጥ ውጤታማ ለመሆን መንግስት የገበያ ትስስር እንዲፈጠርላቸው ጠይቀዋል።

ያመረቱት አፕል ለአረቅጥና ለወልቂጤ ከተማ እያቀረቡ እንደሚገኙ አቶ ሀሺም ተናግረዋል።
በቀጣይ ይበልጥ በስፋት በመስራት ከሀገር አልፎ ለውጭ ሀገር በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ለማስገኘት እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በእርሻ ልማቱ ለወጣቶች የስራ ዕድል መፍጠራቸውን የተናገሩት አቶ ሀሺም ምርጥ ዘር በማባዛት ለአካባቢው አርሶ አደር ከመስጠት ባለፈ ተሞክሮአቸውን እያካፈሉ እንደሚገኙ ጠቅሰው የአካባቢው አርሶ አደር ከእርሻ ልማቱ ተሞክሮ በመውሰድ ባህርዛፍ ከመትከል በመውጣት መሰል ስራዎችን በመስራት ሁለንተናዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ መክረዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ የአካባቢው ተወላጆች ወደ አካባቢያቸው በመምጣት መሰል ስራ በመስራት ውጤታማ መሆን እንደሚችሉ ገልጸዋል።

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ እንዳሉት እንደ ዞን አርሶ አደሩ በፍራፍሬ ራሱን እንዲችል ለማድረግ የአየርጸባይና አቅም በመለየት የተሰሩ ስራዎች ተስፋ ሰጪ ናቸው።

የፍራፍሬ ችግኝ በስፋት በማዘጋጀት ለአርሶ አደሩ በማቅረብ በአጭር አመታት ዞኑ በፍራፍሬ በቂ ምርት እንዲቀርብ ማድረግ እንደሚቻል የጉመር ወረዳ እየሰራው ያለው ስራ ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል።

መንግስት ያወረደው የ30-40-30 የፍራፍሬ ፕሮግራም በዞኑ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ አንድ አርሶ አደር 1መቶ ፍራፍሬ በጓሮው እንዲተክል መደረጉን ገልጸው በዚህም እንደየ አየር ጸባያቸው ተስማሚ የሆኑ ፍራፍሬዎችን ለአርሶ አደሩ በማቅረብ በተደራጀ መንገድ አርሶ አደሩ አፕል፣ ሙዝ፣ አቮካዶ፣ ፖፖያ በስፋት እያመረቱ ይገኛሉ።

በዞኑ በመንግስት፣ በአርሶ አደር፣ በወጣቶችና በሴቶች ማህበራት ችግኝ ማፍያ ማዕከል በዘንድሮ አመት ከ1ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ የፍራፍሬ ችግኝ እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ዞኑ በፍራፍሬ ዘርፍ ፖቴንሺል ከመሆኑም በላይ አርሶ አደሩ የተሰጠውን ምክረሀሳብ በተገቢው ተግባራዊ የሚያደርግ መሆኑን ያነሱት አቶ አበራ ይህ እድል በተገቢው በመጠቀም አርሶ አደሩ በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ በማድረግና ህይወቱን ለመቀየር ሁሉም ርብርብ ሊያደርግ ይገባል ብለዋል።

የበሽመንዳ ልማት ድርጅት እየሰራው ያለው ስራ አበረታች በመሆኑ ይህ ምርጥ ስራ ወደ ሌሎችም አርሶ አደሮች ማስፋት ላይ በትኩረት መስራት እንዳለበት ያነሱት ኃላፊው እየተመረቱ ያሉ ምርቶችን በተገቢው ለገበያ እንዲያቀርቡ የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንደሚሰራ ተናግረዋል።

የጉመር ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ ከድር የበሽመንዳ እርሻ ልማት ባለቤት አቶ ሀሺም ጀማል በወረዳው እንሰሳት ዘርፍ፣ በፍራፍሬ፣ ዘር በማባዛት እየሰሩት ያለው ስራ አበረታች መሆኑን ተናግረዋል።

በወረዳው የ30-40-30 ተግባራዊ በማድረግ አርሶ አደሩ የምግብ ዋስትናቸውን ለማረጋገጥና የኢኮኖሚ ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት በመሰራቱ ውጤታማ መሆን ችሏል ብለዋል።

አርሶ አደሩ በስፋት በማምረቱ ወደ ገበያ በማውጣት ተጠቃሚ እየሆኑ ነው ያሉት አስተዳዳሪው ምርቱ ወደ የገበያ ማዕከል በማውጣት ወረዳው እንዲተዋወቅና አርሶ አደሩ የኢኮኖሚ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንደሚሰራ አስረድተዋል።

የወረዳው ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ደገሙ አለሙ በወረዳው በዘንድሮ አመት በመንግስትና በፕሮጀክት 5ነጥብ 5 ሚሊዮን ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችን እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት የአፕል ችግኝ በርካታ ወጪ፣ ጊዜና ጉልበት በማውጣት ከአርባምንጭ ጨንቻ በማስመጣት ለአርሶ አደሩ ተደራሽ ይደረግ እንደነበር አስታውሰው ይህም ከአርሶ አደሩ ፍላጎት አንጻር ውስነት እንደነበረበት ጠቅሰው ችግሩን ለመቅረፍ በዘንድሮ አመት በወረዳው የአፕል ችግኝ ጣቢያ በማቋቋም ችግኝ በማዘጋጀት የአርሶ አደሩ ከማሰራጨት ባለፉ አርሶ አደሩ ከችግኝ ጣቢያው ልምድ በመውሰድ በጓሮአቸውንና ወጣቱ ተደራጅተው እንዲሰሩ ይሰራል ብለዋል።

ወረዳው የፖምና የፕሪም ፍራፍሬ በስፋት በማምረት የአርሶ አደሩ ሁለንተናዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው በዘንድሮ አመት 6ነጥብ 5 የፖም ችግኝ እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

አቶ ኸይሩ ከድር በበሽመንዳ እርሻ ልማት ድርጅት የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው ሲሆን ከዚህ በፊት ከተማ ይሰሩ እንደነበረና አሁን ላይ የስራ ዕድል ተፈጥሮላቸው በገቢው ቤተሰቦቻቸው እያስተዳደሩ መሆኑን ተናግረዋል።

የስራ እድል ተጠቃሚው አክለውም በእርሻ ልማቱ ለበርካታ ወጣቶች የስራ ዕድል እንደተፈጠረላቸው ጠቁመዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *