መምሪያው የ2016 ዓ.ም የ1ኛ ወሰነ ትምህርት የተማሪዎች ውጤት ግምገማ እና የምክክር መድረክ በወልቂጤ ከተማ አካሂዷል።
የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ መብራቴ ወ/ማረያም እንደተናገሩት የተማሪዎች ውጤት ለመሻሻል በዘርፉ የሚገጥሙ ችግሮች በመለየትና የተጀማመሩ የትምህርት ልማት ስራዎች ማጠናከር እንደሚገባ አስታውቀዋል።
አክለውም የትምህርት ውጤት ለማሻሻል ተማሪዎችን ማብቃት፣የመምህራን ጥቅማ ጥቅም ማስጠበቅ፣የቤተ ሙከራና የቤተ መጽፍት አጠቃቀም ማሻሻል፣የግል ትምህርት ቤቶችን መደገፍ፣ተማሪዎችን የተግባርና የፈጠራ ስራዎቻቸው ላይ ክህሎታቸው እንዲያሳድጉ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል።
በዞኑ ከ3ሺ 200 በላይ ተማሪዎች በተለያዩ ምክንያቶች ዞን አቀፍና መደበኛ ለፈተና አልተቀመጡም ያሉት አቶ መብራቴ ከነዚህ ተማሪዎች ውስጥ በህጋዊ መንገድ ዝውውር የተሰራላቸው በመለየት ከትምህርት ገበታ ውጪ የሆኑት በመለየት ችግሩ በዘላቂነት መፍታት ይገባል ነው ያሉት።
በተከናወነው ያለው የመጽሀፍት ህትመት የሀብት አሰባሰብ ተግባር ከፍተኛ ውጤት መገኘቱና በቀጣይ ህትመቱ አጠናቆ ለተማሪዎች ማድረስ ስራ በትኩረት እንደሚሰራ ገልፀው የተጀመረው የጉራጊኛ ትምህርት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አሳስበዋል።
በዞኑ በእንግሊዝኛ፣በሂሳብና በፊዚክስ ትምህርት ላይ ከፍተኛ የሆነ የመምህራን እጥረት የገጠመ ሲሆን ችግሩን ለመቀነስ ከወልቂጤ ዩኒቨርስቲ ጋር በነዚህ ትም/ት አይነቶች የማጠናከሪያ ትምህርት በተመረጡ ተቋማት መስጠት መጀመሩ ገልፀው ችግሩ በዘላቂነት እስኪፈታ ድረስ የትምህርት ቤት ማህበረሰቡ እያደረጋቸው ባሉ ድጋፎች ሁሉ መጠቀም እንደሚገባም አመላክተዋል።
በተጨማሪም ችግሩን ለመቀነስ በመንግስት ተቋማት ያሉ ብቁ የመንግስት ሰራተኞች በትርፍ ሰአታቸው ፣ የበጎ አድራጊዎች፣ ጎበዝ ተማሪዎች፣ጎበዝ ምህራን ፣የቀድሞ ተማሪ ህብረቶች በማደራጀትና በማቀናጀት በየክላስተሩ መደገፍ ያስፈልጋል ሲሉ መክረዋል።
እንደ አቶ መብራቴ ገለጻ በዞኑ የትምህርት ውጤት ስብራት ለመቀነስ እየተደረገው ያለው ጥረት በፊት ከነበረበት አንጻር አበረታች ለውጦች ያሉ ሲሆን ለአብነትም የዘንድሮ የ6ኛ ክፍል ዞናዊ ውጤት በአማካይ 50 ነጥብ 7 ፐርሰንት፣የ8ኛ ክፍል ዞናዊ ውጤት በአማካይ 36 ፐርሰንት ሲሆን የ12ኛ ክፍል ደግሞ በአማካይ 20 ነጥብ 6 ፐርሰንት ውጤት መመዝገቡ ገልፀው በቀሪ 3 ወራት ተማሪዎች የመደገፍና የማብቃቱ ስራ በተለየ ትኩረት ይመራል ብለዋል።
ቀጣይ ወራት የተማሪዎች ውጤትና ስነ ምግባር እንዲሻሻል በተጀመረው መንገድ ሁሉም ባለድርሻ የበኩሉን መወጣት እንዳለበት አስገንዝበዋል።
አቶ ተጠምቀ በርጋ የእዣ ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ ፣አቶ ሽኩረታ የእኖር ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ እና አቶ ምትኩ ንዳ የዞኑ የወመህ ሰብሳቢ ናቸው።በጋራ በሰጡት ሀሳብ የትምህርት ውጤት ስብራት ለመጠገን ለመጽሀፍት ህትመት ሀብት የማሰባሰብ፣ቲቶርያል የመስጠት፣የውይይት መድረክ የማዘጋጀት፣ከበጎ አድራጊ ድርጅቶች ጋር በቅንጅት እየሰሩ እንደነበር አስታውሰዋል።
ወላጆች ለትምህርት ጥራትና ስነ ምግባር ከፍተኛ ሚና አላቸው ያሉት ሀሳብ ሰጪዎቹ ወላጆች ልጆቻቸው በመቆጣጠር፣የትምህርት ዘርፉን መደገፍና በትምህርት ዘርፉ የሚታዩ ችግሮች ለመቅረፍ በገንዘብ፣በእውቀትና በጉልበት በማገዝ በቀጣይ የሚፈለገው ውጤት እንዲመጣ የበለጠ መስራት እንደሚገባ አንስተዋል።
በዘርፉ የሚሰሩ ስራዎች ጥሩ ቢሆኑም የትምህርት ውጤት ግን በሚፈለገው ልክ ሊመጣ ባለመቻሉ በቀጣይ የተማሪዎች መጠነ ማቋረጥ፣የመምህራን እጥረት፣የትምህርት መሰረተ ልማት አቅርቦት፣የመምህራን የአቅም ውስንነትና ሌሎች ችግሮች ላይ በትኩረት ከተሰራ የትምህርት ውጤት ጥማት በሂደት ማርካት ስለሚቻል በዚህም ኃላፊነታቸው እንደሚወጡ አስታውቋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።