የተማሪዎች ውጤትና ስነ ምግባር በማሻሻል በእውቀትና በክህሎት የዳበረ ሀገር ተረካቢ ትውልድ ለማፍራት በትኩረት እየሰራ እንደሚገኝ የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ አስታወቀ ፡፡

የተማሪዎች ውጤትና ስነ ምግባር ለማሻሻል የሚረዳ የምክክር መድረክ በጉራጌ ዞን በምሁር አክሊል ወረዳ በሐዋሪያት ከተማ የዞንና የወረዳው ባለድርሻ አካላት በተገኙበት ተካሂዷል።

የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ አስከብር ወልዴ በምክክር መድረኩ ላይ ተገኝተው እንዳስታወቁት የትምህርት ዓመራር ክትትል፣ ኃላፊነት እና የተጠያቂነት ስርዓት መጓደል፣ ከቅድመ አንደኛ ክፍል ጀምሮ በትኩረት አለመሰራቱ፣ በተማሪዎች ዘንድ የትምህርት ፍላጎት እና የውድድር መንፈስ መቀዛቀዝ፣ የመምህራን ዝግጅት፣ ብቃት እና ትጋት አነስተኛ መሆን እንዲሁም ሌሎችም ምክንያቶች የተማሪዎች ውጤት አነስተኛ እንዲሆን ማስቻሉ አብረሰርተዋል።

የዚህ ስራ አንዱ አካል የሆነው መድረክ በምሁር አክሊል ወረዳ ለአምስት ተከታታይ ዓመታት የተሰተዋለውን የተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆል ተከትሎ ችግሩን ለመፍታት የዞኑ ትምህርት መምሪያ በወረዳው በተለያዩ ትምህርት ቤቶች ላይ ድጋፍና ክትትል እንዲሁም የሱፐርቪዥን ስራ በመስራት ያሰባሰበው መረጃ በመተንተን ለወረዳው ባለድርሻ አካላት ቀርቦ ችግሮቹ እንዲፈቱ የጋራ መግባባት ተፈጥሯል ብለዋል።

በዞኑ የትምህርት ጥራት ሊያሻሽሉ የሚችሉ ጉዳዮች ትኩረት ተሰጥቷቸው እየተሰራ ይገኛል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ህጻናት በአፍ መፍቻ ቋንቋቸው እንዲማሩ በጉራጊኛ ቋንቋ የሙከራ ትግበራ በ11 ወረዳዎች እና በተመረጡ ት/ቤቶች እየተሰጠ መሆኑንና በ2015 ዓ.ም ወደ ሙሉ ትግበራ ለማስጀመር እንዲቻል ከወዲሁ እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የምሁር አክሊል ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አንዳምላክ ባረጋ እንደገለጹት ለአምስት ተከታታይ አመታት እየቀነሰ የመጣው የተማሪዎች ውጤት ለማሻሻል ስኩልና ብሎክ ግራንት በጀት በአግባቡ እንዲጠቀሙና የተለያዩ ግብዓቶችን እንዲያሟሉ እንዲሁም የመምህራን እውቀትና ክህሎት እንዲዳብር ተገቢውን የድጋፍና ክትትል ስራ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

የተማሪዎች ውጤትና ስነ ምግባር ለማሻሻል የትምህርት ቤት ማህበረሰብና የወረዳው ህብረተሰብ የሚያደርጉትን ንቁ ተሳትፎ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።

አቶ ሺፈራው ወልዴ የተክለሃይማኖት ክላስተር ሱፐርቫይዘር እና አቶ ወሰን ዘርጋው የመገራን ክላስተር ሱፐርቫይዘር ናቸው። ሁለቱም በሰጡት አስተያየት ለተማሪዎች ውጤት ማሽቆልቆል የተማሪዎችና የመምህራን ተነሳሽነት ማነሰ፣ የወላጆች የክትትል ማነስ፣ በምህራን ፍልሰት የሚከሰት የትምህርት ብክነት፣ የቲቶሪያል ትምህርት አለመጠናከር፣ መምህራን ከሰለጠኑበት የትምህርት ዘርፍ ውጪ እንዲያስተምሩ መደረጉ፣ የእውቀትና ክህሎት ማነስ፣ ለቅድመ መደበኛና ከ1ኛ እስከ 4ኛ ክፍል ላሉ ተማሪዎች ላይ መሰረት የሚሆን ስራ አለመሰራት በምክንያትነት ይጠቀሳል ብለዋል። ችግሮቹን ለመቅረፍና የተማሪዎች ውጤት ለማሻሻል ልዩ የአጭር ጊዜና የረጅም ጊዜ እቅድ አቅደው ህብረተሰቡንና ተማሪዎችን በማሳተፍ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

በምክክር መድረኩ ከተሳተፉ ርዕሰ መምህራን መካከል የሀዋሪያት አጠቃላይ 2ኛና መሰናዶ ት/ቤት ርዕሰ መምህር አቶ አስራት ለገሰ እንዳሉት የፕላዝማ ትምህርት፣ ቤተ ሙከራ፣ ቤተ መፅሀፍትና ሌሎች የግብአት አቅርቦት ችግር በመኖሩና የህብረተሰቡ ድጋፍ ማነስ ምክንያት በዞን፣ በክልልና በሀገር አቀፍ ደረጃ በሚሰጡ ፈተናዎች የተማሪዎች ውጤት እየቀነሰ መምጣቱን ተናግረዋል።

አክለውም የዞኑ ትምህርት መምሪያና የወረዳው ትምህርት ጽ/ቤት የተማሪዎች ስነ ምግባርና የፈተና ውጤታቸው እንዲሻሻል ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር መደረጉ ለውጥ ለማምጣት እንደሚያስችል ተናግረው በትምህርት ቤታቸው የሚስተዋሉትን የአፈጻፀም ጉድለቶችን በመለየትና ህብረተሰቡን በማሳተፍ ችግሩን ለመቅረፍ ርብርብ እንደሚያደርጉ ጠቁመዋል።

በምክክር መድረኩ የዞኑ ትምህርት መምሪያ የማኔጅመንት አካላት፣ የምሁር አክሊል ወረዳ ትምህርት ጽ/ቤት ባለሙያዎች፣ ሱፐርቫይዘሮች፣ ርዕሰ መምህራን፣ የወረዳው ከፍተኛ አመራሮች፣ የዞኑ መምህራን ማህበር፣ የዘርፉ የዞን ቋሚ ኮሚቴዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

= ኢትዮጵያን እናልማ!
= የፈረሰውን እንገንባ!
= ለፈተና እንዘጋጅ!

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:- https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *