የብልጽግና ፓርቲ ሊፈጽማቸው ያቀዳቸውና ህዝቡ የሚጠይቃቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ደረጃ በደረጃ ለመመለስ አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ ተገለጸ።

ሰኔ 20/2015 ዓ/ም

የብልጽግና ፓርቲ ሊፈጽማቸው ያቀዳቸውና ህዝቡ የሚጠይቃቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ደረጃ በደረጃ ለመመለስ አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ ተገለጸ።

በጉራጌ ዞን ማዕከል የሚገኙ የፌደራል፣ የክልልና የዞንና የወልቂጤ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ አመራሮች ለ4 ተከታታይ ቀናት በወልቂጤ ከተማ ሲሰጥ የነበረው ስልጠና ተጠናቋል።

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ላጫ ጋሩማ እንዳሉት የብልጽግና ፓርቲ ወደ ስልጣን እንዲመጣ ይዟቸው የተነሳውና በምርጫው ወቅት ለህዝቡ ቃል የገባቸው የልማት ና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ሁሉም ተቀናጅቶ መስራት ይኖርበታል ብለዋል።

እነዚህ ፍላጎቶችን ደረጃ በደረጃ የሚመለሱ ሲሆን የፓርቲው ቀይ መስመር የሆነው ሌብነትንና ብልሹ አሰራሮች ለመቀነስ መንግስት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አስታውቀዋል።

የመንግስት ሰራተኛውና አጠቃላይ ህብረተሰቡ እየተፈታተነ ያለው የኑሮ ውድነት መባባስ፣የማዳበሪያ እጥረት፣ የሰላምና ጸጥታ ጉዳዮች ትኩረት በመስጠት ሊሰራ ይገባል ያሉት አቶ ላጫ ኢኮኖሚያችን ለማሳደግና የኑሮ ውድነቱን ለማረጋጋት የግብርና ስራችን ከምንም ጊዜ በላይ አስበልጠን ልንሰራበት እንደሚገባ አሳስበዋል።

ከዚህ በፊት ችግሮችን ለማሸነፍ የበጋ መስኖ ስንዴ፣የአረንጓዴ አሻራ፣ሜጋ ብሮጀክቶችን ሰርቶ መጨረስና ሌሎችም ተግባራት አበረታች መሆናቸው ተናግረዋል።

ከለውጡ ጊዜ ጀምሮ እያጋጠሙ የነበሩ ችግሮችና የተገኙ ትሩፋቶች ለይቶ በማውጣት በቀጣይ ህብረተሰቡ ከፓርቲው የሚፈልገው ውጤት እንዲመጣ መንግስት በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልና የደቡብ ክልል መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አበባየሁ ታደሰ እንደገለጹት ብልጽግና ፓርቲ ለህዝቡ የገባው ቃል ለመፈጸምና ሀገሪቱ እየገጠማት ያለው ፈተና በድል ለመወጣት እንዲሁም ህዝቡ የሚጠይቃቸው የልማትና የመልካም አስተዳደር ጉዳዮች ደረጃ በደረጃ ለመመለስ አመራሩ በቁርጠኝነት ሊሰራ እንደሚገባ ገልጸዋል።

በተለይ አለም አቀፋዊና ሀገራዊ ተለዋዋጭ ጉዳዮችን ተገንዝቦ አመራሩ በጥበብና በእውቀት መምራት ይኖርበታል ያሉት በየአካባቢው የልማት፣ የመልካም አስተዳደርና የጸጥታ ችግሮች የሚስተዋሉ ሲሆን እነዚህም በእቅድና በውጤታማነት እንዲመሩ ይደረጋል ብለዋል።

ጠንካራ የሆነ ተቋማትና የፍትህ ስርአት መገንባት የግድ በመሆኑ ከታች ጀምሮ በመንግስት ተቋማት የሚሰጡ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርአት በማዘመን ህብረተሰቡ የሚፈልገው ቀልጣፋ አገልግሎት በአግባቡ መስጠት ያስፈልጋል ነው ያሉት።

ህግ የማስከበር፣በፓርቲው ውስጥ ያሉ ብልሹ አሰራሮችን ፈጥኖ የማረምና በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ አፋጣኝ አቅጣጫዎች ለማስቀመጥ በስራ አስፈጻሚውና በማእከላዊ ኮሚቴው አቅጣጫ መቀመጡን ዶ/ር አበባየሁ ተናግሯል።

አቶ ሙራድ ከድር፣ አቶ እንዳለ ስጦታው፣ አቶ አብረሀም ጠና ወይዘሮ መሰረት አመርጋ በጋራ በሰጡት ሀሳብ ከውጭና ከውስጥ ሀገሪቷ እየተፈታተኗት ያሉ ፈተናዎች በድል ለመወጣት አመራሩ ማብቃትና ማሰልጠን ወሳኝነት እንዳለውና ከስልጠናውም በቂ ግንዛቤ እንዳገኙ አመላክቷል።

አክለውም በተወያዩበት ቡድንም የወጣቶች የስራ አጥነት ችግር፣የማዳበርያ አቅርቦት በበቂ ያለመኖር፣የኑሮ ውድነት መባባስ፣ሌብነትና ብልሹ አሰራሮች መበራከትና ሌሎችም የልማትና የመልካም አስተዳደር ክፍተቶች በሰፊው እንደሚስተዋል በሰፊው መነሳቱን ተናግረዋል።

በቀጣይ ከብሄርና ከሀይማኖት የሚነሱ ቅሬታዎች፣የሸገር ከተማና የሸኔ ጉዳይ፣የሜጋ ፕሮጀክቶች የፍትሀዊነት ችግር መንግስት አፋጣኝ ማብራሪያና እልባት እንዲሰጣቸው ሲነሳ እንደነበር ተናግሯል።

በመሆኑም ብልጽግና ፓርቲ የያዛቸው እቅዶች የአሰራር ስልት በመፍጠርና በፍጠን ተግባራዊ ለማድረግና ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ አመራሩ በቁርጠኝነት ከሰራ በሀገር፣በክልል፣ በዞን ብሎም በወረዳ ደረጃ የሚፈለገው ውጤት በአጭር ጊዜ ማምጣት እንደሚቻል አስታውቀው በቀጣይም በአሉበት የስራ ዘርፍ በብቃት ከመምራት ጀምሮ የበኩላቸው ድርሻ እንደሚወጡ አስታውቋል።

በእለቱም በስልጠናው ሲሳተፉ የነበሩ አመራሮች በወልቂጤ ከተማ ችግኝ በመትከል ፕሮግራሙ ተጠናቋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን መንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *