የቡታጅራ አጠቃላይ ሆስፒታልን ወደ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስቲታል ለማሳደግ የሚያስችል ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የሆስቲታሉ ስራ አስኪያጅ አስታወቁ፡፡

ሰኔ 27/2015 ዓ.ም

የቡታጅራ አጠቃላይ ሆስፒታልን ወደ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስቲታል ለማሳደግ የሚያስችል ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ የሆስቲታሉ ስራ አስኪያጅ አስታወቁ፡፡

ሆስቲታሉ ከዩኒቨርስቲ ኦፍ ሚሺገን ባገኘው ድጋፍ የአዋቂ ድንገተኛ፣ የእናቶችና ህጻናት ህክምና ክፍል የያዘ ህንጻ እያስገነባ ይገኛል ፡፡

ግንባታው በሆስፒታሉ የቦርድ አባላት ተጎብኝቷል ፡፡

በጉብኝቱ ወቅት የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አንዱአለም መንግስቱ እንደገለጹት ሆስፒታሉ ሁለት ሚሊዮን ለሚደርሱ የህብረተሰብ ክፍሎት አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡

ሆስፒታሉን ወደ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ደረጃ ለማሳደግ ግብ አስቀምጦ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አቶ አንዱአለም ጠቁመው በዚህም የመሰረተ ልማት ክፍተቶችን ለመሙላት የሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ አዋቅሮ እየሰራ እንደሚገኝ አስታውቀዋል ፡፡

ኮሚቴው በአገር ውስጥና በውጭ ከሚገኙ የአካባቢው ተወላጆችንና ግብረሰናይ ድርጅቶች ለማሳተፍ ባደረገው ጥረት ከዩኒቨርስቲ ኦፍ ሚሺገን የስነተዋልዶ ጤና የስልጠና ማዕከል ጋር የሁለትዮሽ ውል መገባቱን ተናግረዋል ፡፡

ከዩኒቨርስቲ ኦፍ ሚሺገን ጋር በተገባው ውል ለአዋቂ ድንገተኛ እና ለእናቶችናህጻናት የተሟል ህክምና ለመስጠት የሚያስችል በ2 ሺ 530 ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ ህንጻ ግንባታ እየተካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል ፡፡

ግንባታው አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀና ተገቢውን ህክምና መስጠት የሚያስችል እንደሆነ አቶ አንዱአለም ጠቁመው ዩኒቨርሲቲው የህንጻው ግንባታ ሲጠናቀቅ የህክምና መስጫ መሳሪያዎች እንደሚያሟላ ስምምነት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል ፡፡

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪና የቡታጅራ አጠቃላይ ሆስፒታል የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ላጫ ጋሩማ እንደተናገሩት በሆስፒታሉ እየተከናወነ ያለው ግንባታ ሆስፒታሉን ወደ አጠቃላይ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ለማሳደግ የተያዘውን እቅድ ለማሳካት ያስችላል ፡፡

በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ባላቸው ዕውቀትና አቅም በጤናው ዘርፍ ለአገራቸው ድጋፍ እንዲያደርጉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል ፡፡

የሆስፒታሉ ሀብት አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ በቀለ አየለ በበኩላቸው ሆስፒታሉ መሰረቱ የህዘዝብ ተሳትፎ እንደሆነ ተናግረው ኮሚቴው የሆስፒታሉን ደረጃ ለማሳደደግ ህብረተሰቡንና ግብረሰናይ ድርጅቶችን በማሳተፍ እየተንቀሳቀቀሰ ነው፡፡

በሆስፒታሉ እየተከናወነ ያለው ግንባታ በአጭር ጊዜ እንደሚጠናቀቅ የተናገሩት አቶ በቀለ መሟላት ያለባቸው ቀሪ ግብአቶችን ለማሟላት እንደሚንቀሳቀሱ አስታውቀዋል፡፡

የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ሀላፊ አቶ ሰለሞን ጉግሳ የሆስፒታሎች አደረጃጀት በማሳደግ ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት ተገቢ እንደሆነ ተናግረዋል ፡፡

በቡታጅራ አጠቃላይ ሆስፒታል እየተከናወነ ያለው ግንባታ ቀደም ሲል ህዝቡ ሲያነሳ የነበረውን የደረጃ ማሳደግ ጥያቄ የሚመልስና ለህብረተሰቡ የተሟላ ህክምና ከመስጠት በተጨማሪ እንግልትና አላስፈላጊ ወጪ ያስቀራል ብለዋል ሲል የዘገበው የወልቂጤ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *