የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የአብሮነት እሴታችን እንዳይሸረሸር ትልቅ ፋይዳ እንዳለዉ የጌታ ወረዳ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ገለፀ።


የ2016 ዓ.ም የበጋ ወራት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ተጠናክሮ ቀጥሎ በዛሬዉ እለትም በዛራ ቀበሌ በገነት መንደር የአንድ አቅመ ደካማ ቤት ግንባታ ስራ ተሰርቷል፡፡

የበጎ ፍቃድ አገልግሎት የአብይ ኮሚቴ ሰብሳቢና የጌታ ወረዳ ረዳት የመንግስት ተጠሪ አቶ ሀምዱ ንዳ እንዳሉት እንደ ወረዳችን የበጎ ፍቃድ አገልግሎት በልዩ ትኩረት በመሰራቱ በርካታ አቅመ ደካሞችን የቤት ባለቤት ማድረግ ተችሏል ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያውያንን አንድ ከሚያደርጉን ጉዳዮች መካከል አንዱ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ስራችንና የእርስ በርስ መረዳዳት ባህላችን በመሆኑ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ሲሉ አሳስበዋል፡፡

የተጀመረዉን ቤት በተሎ አጠናቆ ለባለቤቱ ለማስረከብ ሁሉም በጋራ መረባረብ እንዳለበትና ቁልፊን ማስረከብ ይኖርብናል በማለት ተናግረዉ በዚህ የቤት ግምባታም 30 ቆርቆሮ እና ለሌሎች ቁሳቁሶች ድጋፍ መደረጉን የተናገሩት አቶ ሀምዱ በቀጣይም ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ድጋፍ እንደሚደረጉም ተናግረዋል።

የጌታ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የወረዳዉ ትምህርት ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ሀብቱ ወ/እየሱስ እንደተናገሩት በሀገራችን ብሎም በወረዳችን ከቅርብ አመታት ወዲህ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ያለ ተግባር በመሆኑ ውጤት ማምጣት ችለናል፡፡

በመቀጠልም የመልካምነትን ጥግ እያየንበት ያለዉ ይህ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዉ በየአካበቢያችን ያሉ ድጋፍ የሚሹ ወገኖቻችን ችላ ሳንላቸዉ ከጎናቸዉ ልንሆን ይገባል ብለዋል።

በዛሬዉ እለትም እየተገነባ ያለዉን ቤት እንደጀመርነዉ በተባበረ ክንዳችን በማጠናቀቅ በአጭር ጊዜ ለባለቤቱ እናስረክባለን ብለዋል።

የጌታ ወረዳ የወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ስንታየው ተሰማ እንዳሉት በዘንድሮ አመት በበጎ ፍቃድ ተግባር ወጣቶች በማስተባበር በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን ገልፀው በተለይም ጧሪ ለሌላቸው ቤት በመስራት፣ እርሻ በማሳረስ፣ በበዓላት ወቅት የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉንና ለረዥም ጊዜ ቤት ውስጥ በጤና ችግር ምክንያት የቆየውንም ወጣት በማስተባበር ለህክምና የመላክ ስራ ተሰርቷል ብለዋል፡፡

በመቀጠልም በዚህ ስራ እየተሳተፋቹ ላሉ ወጣቶች በወረዳው ስም ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበው አሁንም ያልደረስንላቸው በረካታ ወገኖች ስላሉ ሁሉም የተለመደው ትብብር አንዲያደርግ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

የጌታ ወረዳ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽ/ቤት ባለሙያ የሆኑት አቶ ተመስገን ነጋሽ እንዳሉት በበጀት አመቱ በርከታ ድጋፎች መደረጋቸዉን ተናግረዉ እስካሁን የአልባሳት፣ የምግብ እህሎች እንዲሁም ከ60 በላይ ቆርቆሮዎች ድጋፍ ማድረጋቸዉን ገልጸዉ በቀጣይም በተለያዩ ቀበሌዎች ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

በበጎ ፍቃድ አገልግሎቱ የተሳተፉ የአካባቢ ወጣቶችም እንዳሉት እጅግ ደስ የሚል ተግባር ነዉ በእንደዚህ አይነት ተግባር በመሳተፋችንም እድለኞች ነን በማለት ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ባለዉ ጊዜ ከጎናቸው እንደማይለዩና በተቻለን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

ድጋፍ የሚደረግላቸዉ ወ/ሮ ደመቁ ኢባባ እንዳሉት ከዚህ በፊት የነበረዉ ቤት ሙሉ ለሙሉ በመፍረሱና በመዉደቁ ምክንያት ሌላ ቤት እንደሚኖሩ ተናግረዉ አሁን ግን ጸሎቴን ፈጣሪ ሰምቶኝ የቤት ባለቤት ልሆን ነዉ በዚህም ለተደረገላቸዉ ድጋፍም እጅግ መደሰታቸዉን ገልጸዉ ስለተደረገላቸዉ ድጋፍም የወረዳዉን መንግስት ከልብ አመስግነዋል ሲል የዘገበዉ የጌታ ወረዳ መንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ነዉ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *