የቋንጤ ከተማ የእድገት ደረጃ በማሻሻል ለኑሮ አመቺ እና ተመራጭ ለማድረግ በመንግስት እንዲሁም በህብረተሰቡ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የጌታ ወረዳ አስተዳደር አስታወቀ።
በበጀት አመቱ ለከተማው ከ15 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በላይ ተመድቦ ወደ ስራ መገባቱ የጌታ ወረዳ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ጽ/ቤት ገለጸ።
የቋንጤ ከተማ ከተቆረቆረች ብዙ አመታት ብታስቆጥርም የእድሜዋ አክል እድገት ግን ሳታደግ ቆይታለች።
ይሁን እንጂ ከቅርብ አመታት ጀምሮ በህብረተሰቡ እና በመንግስት የጋራ ቅንጅት እና ቁጭት ከተማዋ የእድገት ለውጥ እያሳየች እንደሆነ የተጀማመሩ የመሰረ ልማት ስራዎች ይመሰክራሉ።
የጌታ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪ እና የትምህርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሀብቱ ወ/እየሱስ በወረዳው ያሉ የቀቡል፣የእስኩት እና የቋንጤ ከተሞች ከነበሩበት ዘገምተኛ እንቅስቃሴ ወደ ፈጣን የእድገት ጉዞ እንዲሸጋገሩ የወረዳው መንግስት በቁጭትና በቁርጠኝነት እየሰራ ይገኛል።
ከዚህም የወረዳው መቀመጫ ቋንጤ ከተማ በተለይ ከ2016 ዓ.ም ጀምሮ ከከተማው ነዋሪ፣ከአርሶ አደሩ፣ ከወረዳው ዉጪ ከሚኖሩ ተወላጆች፣ከመንግስት አመራርና ሰራተኛው ጀምሮ በጋራ ከተማው የማልማት ስራ ተጀምሮ በተሰሩ ስራዎች አመርቂ ለውጦች ታይቷል ብለዋል።
በመሆኑም የቋንጤ ከተማ የእድገት ደረጃ በማሻሻል ለኑሮ አመቺ እና ተመራጭ ለማድረግ በመንግስት እንዲሁም በህብረተሰቡ የተጀመሩ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አቶ ሀብቱ አስታውቀዋል።
አክለውም በከተማው የተጀማመሩ የልማት ስራዎች አጠናክሮ በማስቀጠልና ያልተጀማመሩ አዳዲስ የልማት ፕሮጀክቶች በማስጀመር ቋንጤ ከተማ በቅርብ አመታት የፈርጅ 3 ጀረጃ እንድታገኝ በትኩረት እንደሚሰራ አቶ ሀብቱ ተናግረዋል።
በቀጣይ በሁሉም የሀገሪቱ ክፍል ያሉ የወረዳው ተወላጆች ወደ አካባቢያቸው ገብተው እንዲያለሙ የሚያስችል የውይይት መድረክ ለማዘጋጅት መታቀዱ አቶ ሀብቱ ገልጸዋል።
የጌታ ወረዳ ከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ሰይፈ ተመስገን እንዳሉት የህብረተሰቡን አቅም በመጠቀም ሶስቱ ከተሞች እንዲለሙ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ሲሆን መንግስት በቂ መሬት የማዘጋጀት፣የመብራት ዝርጋታ የማስፋፋ፣በጀት የመመደብ፣ ባለሀብቱ እና ህብረተሰቡ የማሳተፍ እና ሌሎችም መስራት ይጠበቃል።
በአለፈው አመትም ከአመራሩና ከመንግስት ሰራተኛው የደሞዝ ተቆራጭ፣ከወረዳው እና ከከተማው ማህበረሰብ እስከ 5 ሚሊየን ብር በማዋጣት የኮብል፣የዲች እና ሌሎች የመሰረተ ልማት ስራዎች የተሰሩ ሲሆን በበጀት አመቱም ከ15 ነጥብ 5 ሚሊየን ብር በጀት ተመድቦ ወደ ስራ መገባቱ አቶ ሰይፈ ተናግረዋል።
አክለውም በከተማው በመንግስትና በህብረተሰቡ የተጀመሩ የልማት ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸው የዲች፣የኮብል፣ጠጠር ማንጠፍ፣ የመንገድ ከፈታ፣የመሬት አቅርቦት፤ የአካባቢና ጽዳትና ውበት እንዲሁም የመብራት ዝርጋታ ስራዎች በትኩረት እንደሚሰራባቸው ለአብነት አንስተዋል።
ለተለያዩ አገልግሎት የሚውል 1 ነጥብ 23 ሄክታር መሬት ካሳ የተከፈለ ሲሆን እስከ 2 ሚሊየን ብር ወጪ በማድረግ የመብራት ማስፋፊያ ስራ ተሰርቷል ነው ያሉት።በቅርቡም በማህበረሰብ እና በመንግስት ተጨማሪ ፖል የማቆም ስራ መጠናቀቁ በማመላከት።
እንደ አቶ ሰይፈ ገለጻ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃና ተጨማሪ የቄራ ግንባታ የማጠናቀቅ ስራ እንዲሁም 2መቶ 50 ሺ የሚሆኑ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች የመትከልና አረንጓዴ አካባቢዎች የማልማት ስራ ተሰርቷል ብለዋል።
የከተማው ፈርጅ ለማሳደግ ነዋሪው እና ህብረተሰቡ በንቃት እየተሳተፈ ነው ያሉት አቶ ሰይፈ በቀጣይም ከተማው በልማት መሰማራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶች ምቹ ሁኔታዎች የተመቻቹ በመሆኑ ኢንቨስት እንዲያደርጉ አቶ ሰይፈ ጥሪ አስተላልፏል።
የጽ/ቤቱ ምክትል እና የማስፈጸም አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አምዴ ጣሰው በበኩላቸው በከተማው የሚሰሩ የልማት ፕሮጀክቶች በጥራትና በፍጥነት እንዲሄዱ ጨምሮ ጨረታዎች የማውጣት፣ክትትልና ቁጥጥር የማድረግ እና እርምጃ የመውሰድ ስራ ተሰርቶ ተግባሩ በታለመለት ጊዜ እየሄደ ይገኛል።
በ2016 የተጀማመሩ ስራዎች እንዲጠናቀቁ የማድረግና በዘንድሮ አመትም የማህበሰቡ ተሳትፎ አጠናክሮ በማስቀጠል እንዲሁም አዳዲስ ስራዎች እንዲጀመሩ በትኩረት እንደሚሰራ አቶ አምዴ ጣሰው አስታውቀዋል።
አቶ በላይ ታክሰማ ፣አቶ ገብሩ ዝርጓ እና አቶ ከበደ ባሜ የቋንጤ ከተማ ነዋሪዎች ሲሆኑ በጋራ በሰጡት ሀሳብ የቋንጤ ከተማ ከተመሰረተች ብዙ አመታት ብታስቆጥርም የእድሜዋ አክል ግን ሳታድግ ቆይታለች ብለዋል።
ይሁን እንጂ በመንግሥትና በህብረተሰቡ የተጀማመሩ ስራዎች በመሳተፍ ቋንጤ ከተማ አቻ ከተሞች የደረሰቡት ደረጃ ለማዳረስና በቀጣይ የከተማ አስተዳርነት እድገት እንድታገኝ በቁርጠኝነት እየሰሩ እንደሆነ ገልጸዋል።
ለአብነትም በጉለበት፣በእውቀት እና በገንዘብ አስተዋጽኦ እያደረጉ እንደሆነ ያመላከቱት ነዋሪዎቹ ከ3 ሺ እስከ 50 ሺ ብር ለከተማው እድገት አስተዋጾኦ እንዳደረጉ አስታውሰዋል።