የቀደምት የጉራጌ አባቶች የባህላዊ ምህንድስና ጥበብ አሻራ የሆነውን ጀፎረ ተንከባክቦና ጠብቆ በማቆየት ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ በትኩረት እየሰራ መሆኑ የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አስታወቀ፡፡

በጉራጌ ዞን በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ጀፎረዎች (ባህላዊ አውራ መንገዶች) የይዞታ ማረጋገጫና ሰርተቪኬት በመስጠት ለማስተዋወቅ እየተሰራ መሆኑን ተገለጸ፡፡

የጉራጌ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ መሰረት አመርጋ በዞኑ በእኖር ወረዳና በጉንችሬ ከተማ አስተዳደር የሚገኙ ጀፎረዎች አሁናዊ ገጽታቸው ለማየት የመስክ ምልከታ ሲያደርጉ እንደገለጹት ጀፎረ (ባህላዊ አውራ መንገድ) የገጠሩ የጉራጌ ብሄረሰብ መኖሪያ ባህላዊ መንደር ሲሆን አመሰራረቱ በአረንጓዴ ተክሎች በተዋቡ ባህላዊ የእደ ጥበብና የኪነ ህንጻ ጥበብ የሚታይባቸው ባህላዊ ጎጆ ቤቶች መሀል የሚገኝ እጅግ ውብና ማራኪ አካባቢ ነው፡፡

ጀፎረ በርካታ ባህላዊና ሀይማኖታዊ ሁነቶች የሚከናወንበት ከቅየሳው ጀምሮ የራሱ ታሪክ ያለው ሲሆን የመንገዱ ስፋት ከ50 እስከ 60 ሜትር የሚደርስ መሆኑንና ማንኛውም የአካባቢው ነዋሪ ግቢውን ለማስፋት ብሎ አጥር ገፋ አድርጎ ማጠር፣ አፈር ቆፍሮ ማስገባት፣ ለቤት መመረጊያ የሚሆን ጭቃ ማቡካትና ቦይ በመቆፈር ጎርፍ ወደ ግቢ እንዲገባ ጨምሮ ምንም ነገር ማድረግ የማይቻል መሆኑንና ይህንንም የሚጠብቁ የሀገር ሽማግሌዎች መኖራቸውን ተናግረዋል፡፡

ከጥንት አባቶች ጀምሮ በትውልድ ቅብብሎሽ ሲወራረስ የመጣ ጀፎረ የሚጠበቅበት በመሀል አካፋዩ ላይ ተለክቶ ቂየ (ጥቁር ድንጋይ) የተተከለ ሲሆን ማንኛውም የአካባቢው ነዋሪ አውቆም ይሁን ሳያውቅ ከጆፎረ ወስዶ የራሱ የመሬት አካል በማድረግ የይዞታ ማረጋገጫ እንኳን ቢያወጣበት ይህንን ያደረገው ማን እንደሆነ በቀላሉ አውቆ እርምጃ ለመውሰድ እንደሚረዳ ኃላፊዋ አብራርተዋል፡፡

በመሆኑም ጀፎረ እጅግ በጣም የተከበረ በደስታና በሀዘን የሚገለገሉበት፣ አባቶች ማህበራዊ ፍትህ የሚሰጡበት፣ እናቶች የአንትሮሽት በዓል የሚያከብሩበት፣ ልጃ ገረዶች በነቆ የሚዝናኑበትና ወጣቶች የገና ጨዋታ የሚጫወቱበት በሀገር በቀል ዛፎች የተከበበና አረንጓዴ በመልበስ የተዋበ አካባቢ ነው፡፡

በዞኑ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ ጀፎረዎች (ባህላዊ አውራ መንገዶች) የይዞታ ማረጋገጫና ሰርተቪኬት በመስጠት ለመጠበቅ፣ ለመንከባከብ፣ ለማስተዋወቅ እና በአለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ለማድረግ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር ተቀናጅተው እየሰሩ መሆናቸውን ወ/ሮ መሰረት አመርጋ የሰጡት መረጃ ያመለክታል፡፡

በጉራጌ ዞን የእኖር ወረዳ ረዳት የመንግስት ተጠሪ አቶ አበበ አገዘ በበኩላቸው በወረዳው ለረጅም ዘመናት ህብረተሰቡ በጥሩ ሁኔታ ጠብቆ ካቆያቸው ጀፎረዎች መካከል የገሀራድና የወሸ የሚጠቀሱ ሲሆን የቀበሌ ተደራሽ መንገዶች ግንባታ በሚከናወንበት ጊዜ በጀፎረዎቹ ላይ ጉዳት እንዳይደርስባቸው የወረዳ አስተዳደሩም ከህብረተሰቡ ጋር በመሆን አስፈላጊውን ጥበቃና እንክብካቤ እንደሚደረግላቸው ገልጸዋል፡፡

ህብረተሰቡ ጀፎረ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በጋራ እንዲገለገሉበት ከተፈቀደው ውጪ በግል ምንም አይነት የልማትም ሆነ የግንባታ ስራ እንዳይሰራበት የሚከለክል ባህላዊ መተዳደሪያ ደንብ ያለ ሲሆን በመንግስት መሰረተ ልማት ለማሟላት በተለይ የማብራትና የውሃ አቅርቦት ግንባታ በሚካሄድበት ጊዜ ከህብረተሰቡ ጋር ተወያይቶ ጀፎረ በማያበላሽ መልኩ በአጥር ጥግ እንደሚያከናውኑ ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

በጉራጌ ዞን የጉንችሬ ከተማ ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ ጽጌ ታደሰ በመስክ ምልከታ ወቅት እንዳሉት ጀፎረ ህብረተሰቡ ለለቅሶ፣ ለሰርግና ለህዝባዊ ክብረዓላት ለማክበር ይገለገሉበታል፣ ህጻናት ኳስ ይጫወቱበታል፣ ከብት ያግዱበታል እንዲሁም ፈረስ ይገሩበታል፡፡

በመሆኑም ህብረተሰቡ ለጆፎረ አስፈላጊውን ጥበቃና እንክብካቤ እንዲያደርግለት ግንዛቤ የመፍጠር ስራ በየጊዜው እንደሚሰሩ ኃላፊዋ አብራርተዋል፡፡

በእኖር ወረዳ የገሃራድና በጉንችሬ ከተማ አስተዳደር የቆጭራ ጀፎረዎች አሁናዊ ይዞታቸው ለማየት የመስክ ምልከታ በሚካሄድበት ወቅት አግኝተን ያነጋገርናቸው የሀገር ሽማግሌዎች እንዳሉት ጀፎረ ቀደምት አባቶች ጊዜው በትክክል በማይታወቅበት ወቅት ዘመናዊ የምህንድስና እውቀት ሳይኖራቸው በደቡብና በሰሜን ጀፎረን መሀል አድርገው ሰው እንዲሰፍር ቀይሰው የሰሩት ለረጅም ዘመናት ህብረተሰቡ ለተለያዩ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አገልግሎት እየተጠቀመበት ይገኛል፡፡

ህብረተሰቡም ጆፎረ ስፋቱና ውበቱ ጠብቆ እንዲቆይ ሀገር በቀል ዛፎች በመትከል፣ የሚያማምሩ ጎጆ ቤቶች በመስራትና ጥሩ አጥር በማጠር የማስዋብ ስራ እየሰሩ መሆናቸውንና በጆፎረ ላይ ግለሰቦች ምንም አይነት ልማት እንዳይሰሩ እንዲሁም ጉዳት እንዳያደርሱ የሚጠበቅበት ውስጠ ደንብ መኖሩን የሀገር ሽማግሌዎች ተናግረዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *