የቀቤና ብሔረሰብ ባህል፣ ቋንቋና ታሪክ በማሳደግ ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ የብሄረሰቡ ተወላጆች የድርሻቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የወረዳው አስተዳደር አስታወቀ።

ለ3ኛው ዙር የቀቤና ብሄረሰብ የታሪክ፣ የባህልና የቋንቋ ሲምፖዚየም በወልቂጤ ከተማ ተካሂዷል።

በወሸርቤ ከተማ ለሚገነባው የወሸርቤ ሆስፒታል የመሰረት ድንጋይ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ በክብርት ወይዘሮ ፋጤ ስርሞሎ ተቀምጧል።

የቀቤና ወረዳ ዋና አስተዳደሪ አቶ ዘይኑ ሻቡዲን በሲፖዚየሙ ላይ ተገኝተው እንዳሉት ከዚህ ቀደም በበጀት እጥረት ምክንያት ሲምፖዚየም ሳይካሄድ መቆየቱን አስታውሰው በዛሬው እለት የባህል ማዕከሉ ምረቃ አካል የሆነው 3ኛ ዙር የብሔረሰቡ የቋንቋ፣ የባህልና የታሪክ ሲምፖዚየም መካሄዱን ገልጸዋል።

የሲምፖዚየሙ መካሄድ ትውልዱ ባህሉን፣ ታሪኩንና ቋንቋውን አውቆ እንዲጠብቅና ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ከዚህም ባለፈ የህዝብ ለህዝብ ትስስር ለማጠናከር የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ መሆኑንም አስተዳዳሪው ገልጸዋል።

በቀጣይ የብሔረሰቡን ባህል ፣ ቋንቋና ታሪክ በማሳደግና የቱሪዝም መዳረሻ ከማድረግ ባለፈ ቋንቋውና ባህሉ ሳይበረዝ ለትውልድ ለማስተላለፍ የብሔረሰቡ ምሁራን በቂ ጥናትና ምርምር ማድረግ እንዳለባቸውና ለዚህም የልማት ማህበሩና የወረዳው አስተዳደር እገዛ እንደሚያደርግም ተናግረዋል።

በሲምፖዚየሙ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት አቶ ኸይሩ አህመዲን እንዳሉት ብሔረሰቡ በሀገር ግንባታ ላይ የነበረው ሚና ከፍተኛ መሆኑን ገልጸው የጥናታዊ ጽሁፉ አላማ ትውልዱ ባህሉንና ታሪኩን በሚገባ ተረድቶ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ያለመ ነው ብለዋል።

የሲምፖዚየሙ መካሄድ ብሔረሰቡ ማንነቱ እንዲያውቅ፣ ቋንቋው ለማሳደግ ከማድረጉም ባለፈ ከሌሎች ብሔረሰቦች ጋር ያለውን መስተጋብርና አንድነቱን ለማጠናከር ይረዳል ብለዋል።

በሲምፖዚየሙ የቀቤና ብሔረሰብ በሀገር ግንባታ፣ የቀቤኒሳ ቋንቋ ማሳደግ እንዲቻል የፊደል ገበታ ከሳባ ወደ ላቲን ቋንቋ በሚልና ሌሎችም ጥናታዊ ጽሁፎችን ቀርቦ ውይይት ተካሂዶባቸዋል።

ከዚህ ባለፈ በወሸርቤ ከተማ ለሚገነባው ሆስፒታል በተቀመጠለት የጊዜ ግደብ እንዲጠናቀቅም አቅጣጫ ተቀምጧል።
የሲምፖዚየሙ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የብሔረሰቡ ባህል፣ ቋንቋና ታሪክ ለማሳደግና ለትውልድ ለማስተላለፍ የሲምፖዚየሙ መካሄድ ከፍተኛ ፋይዳ እንዳለው ተጠቁሟል።

አክለውም የቀቤና ብሄረሰብ ከሌሎች እህትና ወንድም ብሄረሰቦች ጋር ያለው ሁለንተናዊ ግንኙነት እንደሚያጠናክር የተናገሩት አስተያየት ሰጪዎቹ በወረዳው የተጀመረው የልማት እንቅስቃሴ ይበልጥ ውጤታማ ለማድረግ ከልማት ማህበሩ በመቀናጀት የበኩላቸውን እገዛ እንደሚያደርጉም ተናግረዋል።

ሲፓዚየሙ ከኦሮሚያ፣ ከሀረሪ፣ ከሲዳማ ክልሎች፣ ከአጎራባች ዞኖችና ከየም ልዩ ወረዳ የተውጣጡ የሀገር ሽማግሌዎችና የክብር እንግዶች በተገኙበት በድምቀት ተካሂዷል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *