የስራ ዕድል ፈጠራ ስራዎችን በማስፋት በየአካባቢው ያሉትን ስራ አጥ ዜጎች ወደ ስራ እንዲገቡ ለማስቻል ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባ የጉራጌ ዞን ስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዞች ልማት መምሪያ አስታወቀ።

መምሪያው የ2015 በጀት አመት የ10 ወራት እቅድ አፈጻጸም ከባለ ድርሻ አካላት ጋር በወልቂጤ ከተማ የውይይት መድረክ አካሂዷል።

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የስራ ዕድል ፈጠራ ኢንተርፕራይዞች ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሙስጠፋ ሀሰን በውይይት መድረኩ ወቅት እንደገለጹት የስራ ዕድል ፈጠራ ስራዎችን በማስፋት በየአካባቢው ያሉትን ስራ አጥ ዜጎች ወደ ስራ እንዲገቡ ለማስቻል በጋራ መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል ።

አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ከግብርና ወደ ኢንዱስትሪ ለሚደረገው ሽግግር ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስላላቸው በዚህም ዜጎች ተጠቃሚ እንዲሆኑ በትኩረት ይሰራል ብለዋል ።

ስራ አጥ ዜጎችን በሚፈለገው ልክ አደራጅቶ ወደ ስራ ለማስገባት የመሬትና የግብአት አቅርቦት፣የብድር ማመቻቸትና ማስመለስ መሰረታዊ ተግዳሮቶች እንደሆኑ የገለጹት አቶ ሙስጠፋ ሀሰን ለዚህም መሳካት የሚመለከታቸው አካላት በትኩረት መስራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።

እንደ ዞን በ2015 በጀት ዓመት በ10 ወር ውስጥ 47 ሺህ 5 መቶ 29 ስራ አጥ ወጣቶችን ወደስራ ታቅዶ ከ40 ሺህ 8 መቶ በላይ ዜጎችን በከተማና በገጠር ስራ ዕድል ፈጠራ እንዲሁም በአነስተኛና በመካከለኛ ኢንተርፕራይዝ የስራ ዘርፎች የስራ እድል መፈጠሩ ገልጸዋል ።

የውይይቱ ተሳታፊዎች እንደተናገሩት በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን በማረም ስራዎችን ከስራ አጥ ፍላጎትና አቅራቦት ጋር በማጣጣም በቀጣይ የተሻለ ስራ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ገልጸዋል።

ቴክኖሎጂ የሚፈጥሩ አካላትን በማበረታታትና ለማህበረሰቡ አገልግሎት እንዲሰጡ ለማስቻል ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በቅንጅት መሰራት እንዳለበት ተናግረዋል።

አምስት አመት ያለፋቸው ሼዶች እና ከዚህ በፊት የተሰራጩ ብድሮችን እያስመለሱ መሆኑንና ስራው የበለጠ ውጤታማ እንዲሆን በትኩረት እንሰራለን ብለዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *