የሴቶች ፌዴሬሽንና ማህበር መልሶ በማደራጀትና ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር የሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚገባም የጉራጌ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።


የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የጉራጌ ዞን ሴቶች ማህበርና ፌዴሬሽን መልሶ ማደራጀያ መድረክ በወልቂጤ ከተማ ተካሄዷል።
የጉራጌ ዞን ብልጽግና ፓርቲ የአደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ ወይዘሮ አመተረኡፍ ሁሴን እንዳሉት የሴቶች ኢኮኖሚያዊ ፣ማህበራዊና ፖለተካዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አጽኖት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል።

ከቀበሌ ጀምሮ የሴቶች ፌዴሬሽንና ማህበር መልሶ በማደራጀትና ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር የሴቶች ሁለንተናዊ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ እንደሚገባም አመላክተዋል።

የሴቶች ተጠቃሚነት ለማሳደግ ሴቶች በአደረጃጀቶች ታቅፈዉ ትግልና ተሳትፎ ማድረግ አለባቸዉ ብለዉ በመደመር እሳቤ ሴቶችን በተለያዩ ዘርፎች እያስመዘገቡት ያለዉን ዉጤት ማስቀጠል እንዳለባቸዉም አብራርተዋል።

በገጠርና በከተማ ሴቶች ወደ ተሻለ ለዉጥና ፍትሃዊ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በግብርና ፣በስራ ዕድል ፈጠራና በሌሎችም የስራ አማራጮች እንዲሳተፉ እንዲሁም በማህበራዊ ዘርፎች የሴቶች የትምህርት ተሳትፎ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ይገኛል ብለዋል።

ሴቶችን በክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎትና በአረንጓዴ ልማት ስራዎችን ከሌላ ጊዜ በተለየ መልኩ በመሳተፍና ዉጤት ማስመዝገብም እንዳለባቸዉ አሳስበዋል።

የጉራጌ ዞን ሴቶችና ህጻናት ጉዳዮች መምሪያ ሀላፊ ወይዘሮ ነጅቢያ መሀመድ በበኩላቸዉ በዞኑ የሚገኙ ሴቶች የመደራጀት ጠቀሜታን በመረዳት በልማት ህብረትና ጾታን መሰረት ባደረጉ አደረጃጀቶች በመደራጀት የተዛባ አመለካከት ለማስወገድ ፣የሴቶች የንብረት ባለቤትነት መብት እንዲረጋገጥ እየተሰራ እንደሆነም ጠቁመዋል።

ሴቶች በሁሉም የልማት ዘርፎች ተሳፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ እየተሰራ ያለዉን ስራ የበለጠ አጠናክሮ በማስቀጠልና በዘርፉ የሚፈለገዉን ዉጤት ማምጣት እንደሚገባም አስረድተዋል።

የጉራጌ ዞን የሴቶች ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንትና የሴቶች ማህበር ምክትል ሰብሳቢ ወይዘሮ ሊዲያ ሳኒ የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ አጽኖት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሆነም አመላክተዋል።

ሰፊዉን የሴቶች ክፍል በተለያዩ የንቅናቄ መድረኮችና በመደበኛ ተግባራት ላይ በስፋት ተሳታፊና ተጠቃሚ ለማድረግ በየደረጃ የሚገኙ የሴቶች ፌዴሬሽንና ማህበር ወቅቱ በሚፈልገዉ መልኩ መልሶ የማደራጀት ስራ በመስራት ወደ ተግባር እንዲገቡ የማድረጉ ስራ ይሰራል ብለዋል።

ሴቶች በህገወጥ መንገድ ወደ አረብ ሃገር እንዳይሄዱ በወልቂጤ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በተለያየ የሙያ ዘርፎች ሰልጥነው ሲኦሲ በመዉሰድ በህጋዊ መንገድ እንዲሄዱ ለማድረግና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሴቶች በአደረጃጀት ስራዎች ወቅት ግንዛቤ መፍጠር እንዳለባቸዉም ተናገረዋል።

በመድረኩ የተገኙ አንዳንድ ባለድርሻ አካላቶች በሰጡት አስተያየት በሁሉም ዘርፎች እስከ ቀበሌ ድረስ አሰራሩን በመጠበቅ በዘርፉ የሚፈለገዉ ዉጤት በማምጣትና የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነት ማረጋገጥ እንደሚገባም ተናግረዋል።

ጠንካራ ብቃት ያላቸዉ ሴቶች በመምረጥና በዘርፉ የተሻለ ለዉጥና ዉጤት እንዲመጣ ከመቼዉም ጊዜ አበክረዉ እንደሚሰሩም አስታዉቀዋል።

በመጨረሻም የፌዴሬሽንና የማህበር ስራ አስፈጻሚ በአዲስ ተመርጠዉ የማጽደቁም ስራ ተከናዉኗል ሲል የዘገበዉ የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ነዉ።8

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *