የሴቶች መስቀል የጎመን_ክትፎ

መስከረም 13/2015

የሴቶችመስቀልየጎመን_ክትፎ

የመስቀል ዝግጅት ክዋኔዎች ከነሀሴ 12 ጀምሮ ነው። በዚህ ታላቅ በዓል መላ የቤተሰብ አባል የስራ ድርሻ አለው። እናቶች የቆጮ፣ የሚጥሚጣ፣ የቂቤና ሌሎችም ቀላል ግምት የማይሰጣቸው ስራዎች ይሰራሉ። ከስራዎቹ በተለየ መስከረም 14 የሚከውኑት የጎመን ክትፎ ነው። ዕለቱም የሴቶች መስቀል በመባል ይታወቃል ።

የሴቶች መስቀል የእናቶች የሙያ ብቃትና ትጋት የሚታይበት የተለየ ቀን ነው። በዚህ እለት እናቶች በውጆ ባጠራቀሙት ወይም በገዙት ቂቤ የተከሸነና ሌላ የምግብ አይነት የሚያስንቅ ልዩ የጎመን ክትፎ አዘጋጅተው ከተነፋፈቀው ቤተሰብ ጋር በደስታ ማዕዱን ይቋደሳሉ።

በስራ ምክንያት ተራርቆ የነበረ ቤተሰብ ይህች ቀን በጉጉት ይጠብቃታል። ይህች ቀን የትኛውም የጉራጌ ተወላጅ ከአቅም በላይ የሆነ ጉዳይ ካልገጠመው በስተቀር በዋዛ አያልፋትም።

የቤተሰብ የመመራረቅ ጅማሮ ነው። እናት ከአይኗ የራቁ ልጆቿን ወዳጆቻቸው አስከትለው የሆድ ሆዳቸው እያወጉና እየተዝናኑ ማዕዷን እያቋደሰች ሀሴት ታደርጋለች። በዚህ እለት ለሁሉም የቤተሰብ አባልና እንግደሰ እንዲሁም የጎረቤት ልጅ በተዘጋጀላቸው የሸክላ ጣባት በጥረስ የጎመን ክትፎ የሚበላበት ቀን ነው፡፡ የዚህ ቀን ሙሉ ወጪ የሚሸፍኑት ሴቶች ናቸው፡፡

ሴቶች ለፍተው፣ ጥረውና ግረው በራሳቸው ወጪ ያዘጋጁት ማዕድ አይረሴ ትዝታ ስለሚጥል ነው የጉራጌ ተወላጆችና ወዳጆች በናፍቆት የሚጠብቁት።

መስከረም 14 ደንጌሳት/የልጆች ዳመራ ቀን በመባል ይታወቃል። ልጆች በየ በራፉ አነስ ያሉ ደመራ ደምረው በዚህ እለት ያቃጥላሉ። ይህ ደግሞ የበዓሉ ኃይማኖታዊ እንደምታው ለማሳየት ነው።

ደንጌሳት /የዴጛ እሳት / የጎመን ክትፎ እለት/ ማታ በየደጃፉ በልጆች የተደመሩ ዳመራዎች የሚቃጠሉበት ቀን ሲሆን በብሔረሰቡ አጠራር የዴጚያ ኧሳት (የባዮች ኧሳት ቀነ) ይባላል።

ዳመራው ሲቃጠል ሁሉም የቤተሰብ አባላት በዳመራው ዙርያ ከቦ በመቆም ደመራው በችቦ እየለኮሱ ጎረ ጎረ ፣ ጎረ ጎረ… እያሉ ፈጣሪን ለዚህ እለት ላደረስከን ብለው ሲያመሰግኑ ሴቶች ደግሞ በእልልታ ያደምቁታል።

በመቀጠል እለቱ አስመልክቶ የተዘጋጀው የጎመን ክትፎ በጣባት ፣ በጥረስ/ በእንሰት ቅጠል በተዘጋጀ መመገብያ/ እየተበላ ምሽቱ ይደምቃል።

       #መልካም_በዓል‼️

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *