የምግብ ስርአት ማጠናከሪያ (FSRP)ፕሮግራም የአርሶ አደሮች ተጠቃሚነት ለማሳዳግ የሚያደርጋቸው ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ ባለድርሻ አካላት በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተገለፀ።

ሰኔ 24/2015
የምግብ ስርአት ማጠናከሪያ (FSRP)ፕሮግራም የአርሶ አደሮች ተጠቃሚነት ለማሳዳግ የሚያደርጋቸው ተግባራት ውጤታማ እንዲሆኑ ባለድርሻ አካላት በትኩረት መስራት እንደሚጠበቅባቸው ተገለፀ።

የምግብ ስርአት ማጠናከሪያ ፕሮግራም (FSRP) ተጠቃሚ ከሆኑ ወረዳዎች አንዱ ቸሃ ሲሆን የፕሮግራሙ የማስጀመርያ መርሀ ግብር በእምድብር ከተማ ተካሂዷል ።

በፕሮግራሙ ማስጀመሪያ መርሀግብር የተገኙት የክልሉ ግብርና ቢሮ የምግብ ስርአት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ማናጀር አቶ ከድር መሀመድ የምግብ ማጠናከሪያ ፕሮግራም ተጠቃሚ በሆኑ ወረዳዎች ለሰባት አመታት የሚቆይ ሲሆን የምግብ ዋስትና በማረጋገጥ አርሶ አደሮች ተጠቃሚ ለማድረግ ይሰራል ብለዋል።

በመሆኑም ፕሮግራሙ ቀጣይነት እንዲኖረው በወረዳው በግብርናው ዘርፍ የተሻለ አፈጻጸምና የአርሶ አድሩን ኑሮ ለማሻሻል ባለ ድርሻ አካላት በትኩረት መስራት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የቸሀ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጥላሁን ሽምነሳ እንደገለጹት የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ስራዎች መስራት በመቻሉ በርካታ ለውጦች የተመዘገቡ ቢሆንም የህበረተሰቡን ፍላጎት ለማርካት በትጋት መስራት ይገባል ብለዋል።

አርሶ አደሩ የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥ ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ አዳዲስና የተሻሻሉ ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀም እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ዋና አስተዳዳሪው በፕሮግራሙ የተጀመሩ ስራዎች ስኬታማ ለማድረግ አርሶአደሮች፣ የግብርና ባለሙያዎችና አመራሮች በቅንጅት እእንደሚሰሩ አስገንዝበዋል።

ይህ ፕሮግራም ለሰባት ዓመት የሚቆይ ሲሆን በወረዳው ቀጣይነት እንዲኖረው የተሰጡንን ግቦች በማሳካት የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚሰሩ አቶ ጥላሁን ሺምነሳ ገልጸዋል።

የቸሀ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ዮሴፍ ይልማ በበኩላቸው የግብርና እድገት ፕሮግራም (AGp) ባለፉት አመታት በርካታ ዜጎችን በግብርናው ዘርፍ በመሰማራት ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል ብለዋል።

ወረዳው በግብርና እድገት ፕሮግራም ያስመዘገበው ውጤት ከፍተኛ በመሆኑ በምግብ ስርአት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ተጠቃሚ መሆን ችሏል ብለዋል።

ፕሮግራሙ መንግስት ባልደረሰባቸው የልማት መስኮች የሚሰራ መሆኑን የተናገሩት አቶ ዮሴፍ ይልማ ከባለፉት ጊዜያት ልምድ በመውሰድ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት ይሰራል ብለዋል ።

የምግብ ስርአት ማጠናከሪያ ፕሮግራም ግብርናውን በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ጉልህ ሚና ይጫወታል ያሉት አቶ ዮሴፍ ፕሮግራሙ ስኬታማ ለማድረግ ለአርሶ አደሩ ግንዛቤ በመፍጠር ወደ ተግባር እንደሚገባ አስረድተዋል።

የወረዳው የምግብ ስርአት ማጠናከሪያ ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ትግስቱ አንሳ ፕሮግራሙ የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ለማሻሻል ፣ አነስተኛ የመስኖ ልማት ለማስፋፋት ፣የምግብ የገበያ መሰረተ ልማት ማስፋፋትና ሌሎችም በርካታ ተግባራቶች ላይ አተኩሮ ይሰራል ብለዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የግብርናው ባለሙያ ለአርሶ አደሩ ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ በመደገፍና ምርታማ የሆኑ ዘሮችን ማቅረብ እንዳለበት ገልጸዋል ።

የምግብ ስርአት ማጠናከሪያ ፕሮግራም በመምጣቱ መደሰታቸውንና ከባለፈው ከግብርና እድገት ፕሮግራም ለአርሶ አደሩና ለወጣቱ በግብርናው ዘርፍ በርካታ ጥቅሞችን በማስገኘቱ ከዛ የነበረውን ተሞክሮ በመውሰድ በትኩረት እደሚሰሩ ተናግረዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *