የምሁር አክሊል ወረዳ ግብርና ልማት ፅ/ቤት የ2016ዓ.ም የተፋሰስ ልማትና የበልግ የንቅናቄ መድረክ ከወረዳና ከቀበሌ ባለድርሻ አካላት ጋር በወረዳ ማዕከል አካሄደ።

የዘመነ ግብርና ለሚሊዮኖች የስራ ዕድል ዋስትና እንደሚያረጋግጥ፣ ጥምር ግብርና ለምግብ ዋስትና እና የክላስተር ግብርና ልማት ለዘላቂ ምርታማነት የአፈር ጤንነት ለግብርና ግንባታ በሚል መሪ ሀሳቦች መድረኩ ተካሂዷል።

በ2016 የልማት ዘመን የተፋሰስ ልማት ስራ ላይ 44,685 የህብረተሰብ ክፍሎችን በማሳተፍ 8,310ሄ/ር መሬት በ29 ንዑስ የተፋሰስ ልማት ለማልማትና የስራ ዕድል ለመፍጠር ዝግጅት መደረጉ በቀረቡት መወያያ ሰነዶች ተመላክቷል።

እንደ ወረዳችን በሁሉም ንዑስ የተፋሰስ ልማት ቡድን ውጤታማ ለመሆን ሁሉንም ባሳተፈ መልኩ ሊሰራ እንደሚገባ የምሁር አክሊል ወረዳ ግብርና ልማት ፅ/ቤት ዋና ኃላፊ አቶ መኑር ጀማል ገልፀዋል።

ባለፋት አመታት የታዩ ምርጥ ስራዎች በማስቀጠልና በክፍተት የተስተዋሉ ጉዳዮች ወደ ተግባር ከመገባቱ አስቀድሞ ሊስተካከሉ ይገባል ብለው የበልግ ስራዎችን ከየትኛውም ጊዜ አጠናክሮ መስራት ይጠበቃል።

የግብርናውን ስራ በዘመነ መልኩ በመስራት ውጤታማ ለማድረግ በሁሉም ዘርፍ ትኩረት እንደሚያስፈልግ፣ የድንች ምርት ለማሳደግ ቴክኖሎጂን ተግባራዊ ማድረግ፣ ከእንሰት ምርት ከማዘመን እንዲሁም በፍራፍሬ ምርት ወረዳው ያለውን የተፈጥሮ ፀጋ በመጠቀም የ30 40 30 ፕሮጀክት ተግባራዊ ማድረግ ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ይጠበቃል ብለው በተፋሰስ ልማት ውጤታማ ስራም መፈፀም ይኖርብናል ሲሉ አቶ መኑር ጀማል አሳስበዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በ2015/16 የምርትና የልማት ዘመን በሁሉም ዘርፎች የተሰሩ ስራዎች እንደተሞክሮ በመውሰድ በ2016/17 የምርትና የልማት ዘመን በተጠናከረ መልኩ መምራትና ውጤታማ ስራ ሊሰራ ይገባል ብለው ለውጤታማነቱ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩሉን ሚና ሊወጣ ይገባል ሲል ተሳታፊዎች አሳስበዋል።

በመድረኩ የተገኙት የጉራጌ ዞን ፕላን ልማት መምሪያ ኃላፊ እና የምሁር አክሊል ወረዳ ደጋፊ አመራር የሆኑት አቶ ከበደ ኃይሌ የተፋሰስ ልማት ስራውን ውጤታማ ለማድረግ ከቅድመ ዝግጅት ጀምሮ በትኩረት መስራት እንደሚያስፈልግ እና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ማሳተፍ ይጠበቃል ሲሉ ተናግረዋል።

እንደ ኃላፊው ገለፃ የግብርና ስራ በዘመናዊ መልኩ ቴክኖሎጂ በመጠቀም መስራት እንደሚጠበቅ አንስተው ከተፋሰስ ልማት ስራ ጎን ሌሎችም ተግባራት አቀናጅቶ መስራት ከሁሉም ይጠበቃል ብለዋል።

አቶ ከበደ አክለው እንዳመላከቱት ከእንስሳት ሃብት፣ ከፍራፍሬ እና በአትክልት ምርት ያለው ተፈጥሮዓዊ ፀጋ በመለየት በሁሉም ቀበሌ መስራት ይጠበቅብናል ብለው የሌማት ትሩፋት ስራችን ውጤታማ ለማድረግ ከእቅድ ጀምሮ በትኩረት መስራት ይገባል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ከእዳ ወደ ምንዳ የምናደርገው ጉዞ እውን ለማድረግ በግብርና ልማት ስራዎች ውጤታማ ልሆን ይገባል ሲሉ የምሁር አክሊል ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ብስራት ገብሩ ገልፀዋል።

የተቀናጀ የግብርና ልማት ስራ ከተለመደው አሰራር በመውጣት ሊሰራ እንደሚገባ፣ ወቅቱን የዋጀ ስራ በመስራት አርሶ አደሩ ውጤታማ ማድረግ ከሁሉም ባለድርሻ አካል የሚጠበቅ ተግባር ነው ብለዋል።

አቶ ብስራት አክለው ለውጤታማነቱ የተሳለጠ የግብርና ቅንጅታዊ አሰራር ማዘመን እንደሚያስፈልግ፣ በበልግ ስራዎች መሳተፍ፣ በዶሮ እርባታ፣ በማሞከት፣ በማድለብ፣ ንብ በማነብ፣ በእንስሳት ተዋፅኦ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

በተፈጥሮ ሃብት የሚሰሩ ስራዎች ለአብነትም የተፋሰስ ልማት ስራን ትኩረት ሰጥቶ መስራት ያስፈልጋል ብለው ወረዳችን በሁሉም የግብርናው ዘርፍ ውጤታማ ስራ ሰርተን አርሶ አደራችን ተጠቃሚ ልናደርግ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።

አቶ ብስራት ገብሩ በማጠቃለያ ሀሳባቸው በወረዳ የተጀመሩ ስራዎች ጥራታቸው በጠበቀ መልኩ በማከናወን እና በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ በማጠናቀቅ የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይኖርብናል ብለዋል።

ዘገባው የወረዳው የመንግስት ኮምዩኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ነው።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *