የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልላዊ መምህራን ማህበር የ1ኛ ሩብ አመት አፈጻጸም ግምገማ እና የምክክር መድረክ በወልቂጤ ከተማ አካሄዷል።
በምክክር መድረኩ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መምህራን ማህበር ሀላፊ አቶ በርታ ያረቢ እንዳሉት ማህበሩ በ2017 ዓ.ም በሩብ አመቱ ለማከናወን የያዝናቸዉ ግቦች ስኬታማ ከፍተኛ ርብርብ በማድረግ ዉጤታማ ስራ ተሰርቷል።
መንግስትና መንግስታዊ ላልሆኑ ድርጅቶች ፕሮጀክት በመቅረጽና በማዘጋጀት የማሰራጨት በመስራት የአባላት ፈሰስ ገቢ በማድረግ የክትትልና ድጋፍ ስራም አጠናክረዉ እየሰሩ እንደሆነም አመላክተዋል።
ለ10 የማህበር መዋቀሮች ማህበሩ በፕሮጀክት በማስደገፍ የፋይናንስ አቅማቸዉን ለማሳደግ በተሰራዉ ስራ አንዳንድ ዞኖች ዉጤታማ እንደሆኑም አብራርተዋል።
በአባላት በሚገኝ ገቢ ብቻ ማህበራት ማንቀሳቀስ አይቻልም ያሉት ሀላፊዉ በፕሮጀክቶች በማስደገፍ የሀላባና የጉራጌ ዞኖች ዉጤታማ መሆናቸዉም አመላክተዋል።
በክልሉ የሚገኙ አባላት በሩብ አመቱ የማጣራት ስራ መጀመሩም አስረድተዉ እነዚህም በትምህርት ዝግጅትና በጾታ ተለይቶ ተሰርቷል።
የመምህራን ደሞዝና ጥቅማ ጥቅም እንዲጠበቅ ልዩ ትኩረት በመስጠት ከሚመለከታቸዉ አካላት ጋር በተለያዩ ጊዜያት ዉይይት የማድረግ ስራም እየተሰራ እንደሆነም አስረድተዋል።
በምክክር መድረኩ ተገኝተዉ ንግግር ያደረጉት የጉራጌ ዞን ትምህርት መምሪያ ሀላፊ አቶ መብራቴ ወልደማሪያም እንዳሉት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል መምህራን ማህበር በክልሉ የገጠመዉን የትምህርት የዉጤት ስብራት ችግር ለመቅረፍ እያደረገዉ ያለዉን ጥረት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስረድተዋል።
መምህራኑ በየደረጃዉ ጥናትና ምርምር በማድረግ የዉጤት ስብራቱን ችግር ሊፈቱ የሚችሉ ስራዎች አጽኖት ሰጥተዉ ሊሰሩበት እንደሚገባም አስረድተዋል።
በዞኑ የሚገኘዉ የሙያ ማህበሩ ከ8 ሺህ በላይ መምህራን ይዞ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን ከዞኑ አስተዳደር ፣ከዞኑ ትምህርት መምመሪያ ጋር በቅርበት በቅንጅት የበጀት ድጋፍ እየተደረገለት እየሰራ እንደሆነም አመላክተዋል።
በዞኑ ለመምህራኖች የደሞዝ መሻሻል ፣የደረጃ እድገትና የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች የማስጠበቅና የማስከበር ስራ ከሙያ ማህበሩ ጋር በቅንጅት እየተሰራም እንደሆነም አመላክተዋል።
በምክክር መድረኩ የተገኙት የጉራጌ ዞን መምህራን ማህበር ሰብሳቢ አቶ ደጀኔ እስጢፋኖስና የከንባታ ዞን መምህራን ማህበር ሊቀመንበር አቶ አለሙ አቡዬ እንዳሉት ባለፈዉ ሩብ አመት የትምህርት ቤቶች የማስጀመር የዝግጅት ስራዎች፣ የመጻሐፍ ተማሪ ጥምርታ ለሟሟላት፣ የወላጆችና የህብረተሰቡን ተሳትፎ እንዲያደርግ የቅስቀሳ ስራ ፣ የመምህራን ጥቅማ ጥቅም ለማስጠበቅና ዘርፈ ብዙ ተግባራት ማከናወን መቻላቸዉም አመላክተዋል።
የትምህርት ጥራት ለማረጋገጥና የተማሪዎች ዉጤት ለማሻሻል የተማሪዎች የግብአት አቅርቦት እጥረት ለመፍታት በርካታ ተግባራት ሲያከናዉኑ እንደነበረም አስረድተዉ ከትምህርት መምሪያዎች ጋር ቅንጅት በመፍጠር ከተማሪዎች ቅበላ ጀምሮ በርካታ ስራዎች መስራታቸዉም ጠቁመዋል ሲል የዘገበዉ የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚኒኬሽን መምሪያ ነዉ።