የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አባላት ቀልጣፋና ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የጤና ተቋማት ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደሚጠበቅባቸው የጉራጌ ዞን አስተዳደር አስታወቀ ፡፡

የዞኑ የ2014 በጀት አመት የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ስራ አፈፃፀም በወልቂጤ ከተማ ተገመገመ ፡፡

የጉራጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ጀማል በመድረኩ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አባላት በጤና ተቋማት ቀልጣፋና ጥራት ያለው የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የጤና ተቋማት የአንድ መስኮት አገልግሎት መስጠት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

አባላቱ በጤና ተቋማት የሚያገኙት ቀልጣፋና ጥራት ያለው አገልግሎት የአባላት ምጣኔ ከማሳደግ ባለፈ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡

ባለፉት ወራት በተከናወኑ ተግባራት በዘርፉ ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበ ሲሆን ለውጤታማነቱ ደግሞ አመራሩና ባለሙያው ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱ እንደሆነም አስረድተዋል።

አክለውም አቶ መሀመድ አንዳንድ መዋቅሮች ማዐጤመን ውጤታማ ለማድረግ ከተሰጣቸው ተልዕኮ በላይ በመስራት ህብረተሰቡ ተጠቃሚ እያደረጉ ይገኛሉ ብለዋል።

በመሆኑም የዘርፉ ውጤታማነት ይበልጥ ለማረጋገጥ የመረጃ አያያዝ፣ የድሃ ድሃ ልየታ፣ የኦዲት ስራ እና ለጤና ተቋማት የአገልግሎት ክፍያ በወቅቱ የመክፈል ስራ ማጠናከር እንደሚገባ አቶ መሀመድ አሳስበዋል።

የጉራጌ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ሸምሱ አማን በበኩላቸው በዞኑ በማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ተጠቃሚ ለማድረግ በተደረገው ጥረት የአባላት ምጣኔ ሽፋን ከነበረበት ዝቅተኛ አፈጻጸም በበጀት አመቱ ወደ 76 በመቶ ከፍ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

እንደ ኃላፊው ገለጻ የማህበረሰብ አቅፍ የጤና መድህን ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ተደራሽነት ለማረጋገጥ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ የጤና ተቋማት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ይደረጋል ።

ዞኑ ሞዴል ለማድረግ ወረዳዎች እና የከተማ አስተዳደሮች የሚጠበቅባቸውን መስፈርቶች ማሟላት ይጠበቅባቸዋል ያሉት አቶ ሸምሱ ወረዳዎች ሞዴል ለማድረግ ከተቀመጠው አፈጻጸም 30 በመቶ የሚሆነው የማዐጤመ አተገባበር በመሆኑ የተለየ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል ብለዋል።

አያይዘውም ኃላፊው ህብረተሰቡ ሳይጉላላ በአቅራቢያው የህክምና አገልግሎት እንዲያገኝ ለማስቻል የወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በማዐጤመ አገልግሎት አሰጣጥ ከወራቤ ኮምፕሬንሲቭ ሆስፒታል ልምድ እንዲወስድ መደረጉንም አቶ ሸምሱ ተናግረዋል።

የጤና ተቋማት የአገልግሎት ክፍያ ሲጠይቁ በወቅቱ መክፈል ይገባል ያሉት ኃላፊው ክፍያው በወቅቱ መፈጸም ተቋማቱ የመድሀኒት አቅርቦት እጥረት እንዳይገጥማቸው ይረዳል ብለዋል።

በመምሪያው የህክምና አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር እና የማዐጤመ አስተባባሪ አቶ አየነው በሪሁን ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት በአዲስ አባላት ክፍያ፣ በአባላት መዋጮ፣ በደረሰኝ አመላለስ እና በአባላት ምጣኔ የተሻለ አፈጻጸም ካስመዘገቡ መዋቅሮች ቸሀ፣ ሶዶና ምስራቅ መስቃን ወረዳዎችና ቡታጅራና ወልቂጤ ከተማ አስተዳደሮች ይገኙበታል ብለዋል።

በእነዚህ ተግባራት ዝቅተኛ አፈጻጸም ያላቸው መዋቅሮች በቀጣይ ክፍተቶቻቸው በመሙላት የማህበረሰቡ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ ይጠበቅባቸዋል ብለዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት ማህበረሰቡ በጤናው ዘርፍ ተጠቃሚ ለማድረግ የማዐጤመ አፈጻጸም ማሳደግ ይገባል ብለዋል።

ባለፉት ወራት በማዐጤመ የተሻለ ውጤት ቢመዘገብም አፈጻጸሙ በሚፈለገው ደረጃ ለማድረስ በቀጣይ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩም ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል።

አያይዘውም ተሳታፊዎቹ በመዋቅሮቹ መካከል የሚስተዋለው የአፈጻጸም ልዩነት ማጥበብ እንደሚገባም አሳስበዋል ሲል የዘገበው የጉራጌ ዞን የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ነው።

= ኢትዮጵያን እናልማ!
= የፈረሰውን እንገንባ!
= ለፈተና እንዘጋጅ!
በመረጃ ምንጭነት ገፃችን ስለምትከታተሉ እናመሰግናለን!

በተጨማሪም እነዚህ ሊንኮችን በመጫን ወቅታዊና ትኩስ መረጃዎቻችንን እንድትከታተሉ እንጋብዛለን፡፡
Facebook:-
https://www.facebook.com/gurage1Zone
Website:- https://gurage.gov.et
Telegram:- https://t.me/comminuca
Youtub: -https://www.youtube.com/channel/UCzrcazGvvIO2tG7bQN36Cx!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *